ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሰሎሞን የጥበብ ጥም ነገሥታት ጥበብን ይቅሰሙ 1 ነገሥታት ሆይ እንዲገባችሁ አድምጡ፤ እናንተ ሥልጣናችሁ እስከ ምድር ዳርቻ የሚደርስ ተመከሩ፤ 2 ታላላቅ ሕዝቦችን የምትመሩ፥ ባስገበራችኋቸው ሀገሮች ብዛት የምትታበዩ፥ እናንተ ሁላችሁ ስሙ 3 ነጻነትን የሰጣችሁ ጌታ፥ ኃይልንም ሰጥቷችኋልና፤ እርሱ ራሱ ድረጊቶቻችሁን ይመረምራል፤ ዕቅዶቻችሁንም ይከታተላል። 4 የመንግሥቱ አገልጋዮች እንደ መሆናችሁ፥ በትክክል ካላስተዳደራችሁ፥ ሕጉን ካላከበራችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ካልፈጸማችሁ፥ 5 በአስፈሪ ሁኔታ ፈጥኖ ይነሣባችኋል፤ በባለሥልጣናቱም ላይ ብርቱ ፍርድ ይሰጣል። 6 የበታች ሹሞች ይታዘንላቸዋል፤ ይቅርታም ይደረግላቸዋል፤ ኃያላኑ ግን ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ። 7 የሁሉም ጌታ ማንንም አይፈራምና፥ ታላቅነት እርሱን አያስደነግጠውም፤ ትንሹንና ትልቁን የፈጠረ፥ ለሁሉም የሚፈልገውን የሚሰጥ እርሱ ነውና። 8 በሥልጣናቸው የሚጠቀሙ ግን ታላቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል፥ 9 እናንተ ነገሥታታ፥ ንግግሬ ሁሉ ለእናንተ ነው፤ ጥበብን ተማሩ፥ ራሳችሁንም ከውድቀት አድኑ። 10 የተቀደሱትን ሕጐች በቅድስና የሚጠብቁ፥ ቅዱሳን ይባላሉ፤ ከእነርሱ መማር በውስጣቸው ያለውን መከላከያም ማወቅ ነው። 11 ስለዚህ የምናገረውን ልብ በሉ፤ በተመስጦ አድምጡ፤ ትምህርት ታገኛላችሁ፤ ጥበብንም የፈለገ ያገኛታል። 12 ጥበብ አንጸባራቂ ናት፤ ምንጊዜም አትደበዝዝም፤ ለሚያፈቅሯት በቀላሉ ትታያለች፤ ለሚፈልጓትም በቀላሉ ትገኛለች። 13 ለሚሿት ሁሉ አስቀድማ ራሷን ታስተዋውቃለች፤ 14 እርሷን ፍለጋ ማልዶ የተነሣ፥ ችግር አያጋጥመውም፤ ጥበብን መሻት ጥበብን ማግኘት 15 እርሷን ማሰላሰል ፍጹም ማስተዋል ነው፤ እርሷን ፍለጋ እንቅልፍ ያጣ፥ ከጥበቃ ፈጥኖ ይወጣል። 16 የእርሷ የሆኑትን ሁሉ ትጠብቃቸዋለችና፤ በመንገዶቻቸው ላይ በቅንነት ትገለጥላቸዋለች፤ ሐሳቦቻቸውንም ታውቃለች። 17 የጥበብ መነሻዋ ከልብ የመነጨ የመማር ፍላጐት ነው፤ የመማር ጉጉት እርሷን ማፍቀር ነው፤ 18 እርሷን ማፍቀር ማለት ሕጐቿን ማክበር ማለት ነው። ሕጐቿን መጠበቅ አለመበላሸትን ማረጋገጥ ነው። 19 አለመበላሸት ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ 20 ስለዚህ ጥበብ መሻት ራስን ወደመግዛት ይመራል። 21 እናንተ ነገሥታት ሆይ፥ ዙፋናችሁንና በትረ መንግሥታችሁን የምትወዱ ከሆነ፥ ጥበብን አክብሩ፤ አገዛዛችሁም ዘላለማዊ ይሆናል። 22 የጥበብን ምንነትና አፈጣጠር ቀጥዬ አብራራለሁ፤ ምንም ምሥጢር አልደብቃችሁም፤ ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ዕድገቷን እገልጻለሁ፤ ስለ እርሷ የምናውቀውን ሁሉ ይፋ አደርጋለሁ፤ ከእውነት ግን አልርቅም። 23 ከሚያቃጥል ምቀኝነት ጋር ወዳጅነት የለኝም፤ ምቀኝነትን ከጥበብ የሚያገናኝ ከቶውንም የለምና። 24 የዓለም ደኀንነት የሚረጋገጠው፥ የጥበበኞች ቍጥር ሲበዛ ነው፤ የሕዝቦች ሰላምም እንዲሁ የሚረጋጠው፥ በንጉሡ ብልኀ አስተዳደር ነው። 25 እንግዲያስ ከቃሌ ተማሩ፤ ጥቅሙም ለእናንተ ነው። |