ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ጻድቁ ግን በድፍረት ይቆማል፤ ጨቋኞቹን ግንባሩን ሳያጥፍ ይመለከታል፥ ስላሳለፈው መከራም አያስብም። 2 እርሱን ባዩ ጊዜ ኃጥአን በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ፤ ባልተጠበቀ ሁኔታም በመዳኑ ይደነቃሉ። 3 በጸጸት እየተቃጠሉ፥ ሢቃ እየተናነቃቸው፥ ትንፋሻቸው ቁርጥ ቁርጥ እያለ እንዲህ ይባባላሉ፥ 4 ስንሳለቅበት የነበረው እርሱ ነው፤ እናላግጥበትም ነበር፤ ምንኛ ተሞኝተናል፤ ሕይወቱን እንደ እብደት፥ አሟሟቱንም ወራዳ አድረገን ቆጥረን ነበር። 5 እንደምን ከእግዚአብሔር ልጆች እንደ አንዱ ሊቆጠር ቻለ? ዕጣውስ ከቅዱሳን ጋር እንደምን ተመሳሰለ? 6 በእርግጥም ከእውነት መንገድ ወጥተናል፤ የፍትሕ ብርሃን ለእኛ አላበራልንም፤ ፀሐይም አልወጣችልንም። 7 እኛ ያልተጓዝንበት የጥፋትና የክፋት መንገድ የለም፤ መንገድ በሌለበት በረሃ አቋርጠናል፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ግን አናውቀውም ነበር። 8 ግትርነት ምን ጠቀመን? ሀብትስ ሆነ ትዕቢት ምን በጀን? 9 እኒያ ሁሉ ክፉ ሥራዎች እንደ ጥላ፥ እንደ በራሪ ወሬም አለፉ። 10 የክፉ ሞገድን ሰንጥቆ ሲያልፍ፥ ያለፈበትን መንገድ ዱካ እንደማይተውና ደጋፊ ብረቱም ላይ አሻራውን እንደማያሳርፍ መርከብ ነው። 11 ወይም በአየር ላይ እንደምትበር፥ ስለ ማለፍዋ ግን ማስረጃ እንደማትተው ወፍም ሊሆን ይችላል፤ ወፍዋ አየሩን በክንፎቿ ትቀዝፋለች፥ ከኋላዋ ግን ስለ ማለፍዋ ምልክት የለም። 12 ወይም በአንድ ኢላማ ላይ የወረወረ ፍላጻ በስቶት ያለፈው አየር መልሶ እንደሚገጥም፥ ፍላጻውም በየትኛው አቅጣጫ እንደተወረወረ ለማወቅ እንደማይቻለው ዓይነት ነው። 13 እኛም እንዲሁ ነን፤ ከመወለዳችን እንጠፋለን፤ መልካም ሥነ ምግባር የለንም፤ በክፉ ሥራችን ተውጠን ጠፍተናል። 14 የክፉ ሰው ተስፋ ነፍስ እንደወሰደው ገለባ፥ ማዕበል እንደገፋው ረቂቅ ውሃ፥ ነፋስ እንደበተነው ጢስ፥ እንደ አንድ ቀን እንግዳ ትዝታ ወዲያው ይጠፋል። አስደሳቹ የጻድቃን ፍጻሜና የኃጥአን ቅጣት 15 ጻድቃን ግን ለዘለዓለም ይኖራሉ፤ ካሣቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ እርሱ ይጠብቃቸዋል፤ 16 ታላቁን ዘውድ ይደፋሉ፤ ከጌታ እጅ የውበትን አክሊል ይቀበላሉ፤ በቀኝ እጁ ይጠብቃቸዋል፤ በክንዱም ይከልላቸዋልና። 17 ቀናተኛ ፍቅሩ ትጥቅ ነው፤ ጠላቶቹን ለመቅጣት ፍጡራንን ሁሉ ያስታጥቃል። 18 ፍትሕና ጥሩር፥ የማያዳግመውን ቀናተኛ ፍርዱን፥ የራስ ቁር ያደርገዋል፤ 19 የማይታጠፈውን ቅድስና ጋሻ፥ የማይበርድ ቁጣውን ሠይፍ ያደርጋል፤ ዓለምም ግድየለሾችን ለመውጋት አብራው ትዘምታለች። 20 በሚገባ የታለሙት ጨረሮች፥ እኒያ መብረቃዊ ጦሮች ይወነጨፋሉ፤ 21 በደምብ ከተወጠረ ቀስት፥ እንደሚምዘገዘግ ፍላጻም፥ ከደመናዎች ውስጥ ኢላማቸውን ለመምታት ይፈተለካሉ። 22 ወስፈንጠሩ በቁጣ የተሞሉ በረዶዎችን ያዘንባል፤ የባሕር ውሃዎች በእነርሱ ላይ ይነሳሉ፤ ወንዞችም ያለ ምሕረት ያጥለቀልቋቸዋል። 23 ኃይለኛ ነፋስ በእነርሱ ላይ ይነፍሳል፤ እንደ ዓውሎ ነፋስም ያበጥራቸዋል። ኃጢአት ምድርን ወና ያስቀራታል፤ ክፋትም የኃያላኑ ዙፋን ያነኳኩተዋል። |