ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ልጅ ባይወልዱም እንካን የመልካም ምግባር ባለቤት መሆን፥ በእግዚአብሔር በሰውም ዘንድ እውቅና ስላለው፥ የማይሞት መታሰቢያ ማቆም ነው። 2 ካገኘነው እርሱን እንከተላለን፤ ካጣነውም እንናፍቀዋለን። ተፋልሞ ያሸንፋል፤ የአሸናፊነቱን ዘውድ ይደፋል፤ ዘላለማዊ ድልንም ይቀዳጃል። 3 ነገር ግን የክፉዎች ልጆች ብዛት እርባና የለውም፤ ዲቃላዎች ስለሆኑም ሥር አይሰዱም፤ ጽኑ መሠረትም አያኖሩም። 4 ለጊዜው ቅርንጨፎች ሊያበቅሉ ይችላሉ፤ መሠረታቸው የጸና ባለመሆኑ ነፋስ ያናጋቸዋል፤ በማዕበሉም ኃይል ተነቃቅለው ይጠፋሉ። 5 ቅርንጫፎቻቸው በለጋነታቸው ይሰባበራል፤ ፍሬያቸው ዋጋ ቢስ፥ ያልበሰለና፥ ለምንም የማይጠቅም ይሆናል። 6 ከሕግ ውጭ የተወለዱ ልጆች፥ በፍርድ ቀን የወላጆቸቸውን ክፋት ይመሰክራሉና። የጻድቃን ዕድሜ ማጠር 7 ጻድቅ ሰው ያለ ዕድሜው ቢሞትም፥ ዕረፍትን ያገኛል። 8 የዕድሜ መርዘም ሽምግልናን አያስከብረውም፤ የዓመታት መብዛትም የሕይወት ትክክለኛ መለኪያ አይደለም። 9 ሽበትስ የሰው ዕውቀቱ ነው፤ ሽምግልናም ያላደፈ ሕይወት ነው። 10 እግዚአብሔርን ስላስደሰተ ተወደደ፤ በኃጢአተኞች መካከልም ስለሚኖር ተወሰደ። 11 ክፋት ከሐሳቡ እንዳያዘናጋው፥ ተንኮልም ነፍሱን እንዳያታልላት እርሱ ተወሰደ። 12 ክፋት መልካም ነገሮችን ያጠላባቸዋል፤ መቋጫ የሌለው ፍላጐትም ንጹሑን ልብ ያበላሻል። 13 ፈጥኖ ፍጹም በመሆኑ ብዙ ኖሯል፤ 14 ነፍሱ ጌታን የምታስደስት በመሆኗ፥ ከከበባት ክፋት ፈጥና ወጣች፤ ሰዎች ግን ሁኔታዋን አልተረዱም፤ አእምሮአቸውም እውነታዋን አልተቀበለውም። 15 የተመረጡት ሁሉ፥ ክብርና ምሕረት እንደሚጠብቃቸው፥ እርሱም ስለ እነርሱ እንደሚሟገት አልተከሠተለትም። 16 ቋሚውን ኃጢአተኛ፥ ፍጹምነትን ፈጥኖ ያገኘ ወጣት፥ ኃጢአተኛውን ሽማግሌ ይፈርድበታል። 17 እኒህ ኃጢአተኞች፥ የጠቢቡን ፍጻሜ ይመለከታሉ፤ ጌታ ለእርሱ ያሰበለትን ግን ከቶውንም አያውቁም፤ ከምንም እንዳዳነው አይረዱም። 18 በንቀትም ይመለከታሉ፤ ጌታ ግን ይሥቅባቸዋል። 19 ፈጥነውም ክብሩን ያጣ ሬሳ ይሆናሉ፤ በሙታንም መካከል ዘላለማዊ ማስፈራርያ ይሆናሉ። እርሱ ይሰባብራቸዋል፤ በጭንቅላታቸው ያሽቀነጥራቸዋል፤ እነርሱም ይደነዝዛሉ። ከመሠረታቸው ያናጋቸዋል፤ ወና ይሆናሉ፤ ኀዘን ይነግሥባቸዋል፤ መታሰቢያቸውም ሁሉ ይጠፋል። ክፉዎች ሲፈረድባቸው፥ 20 ኃጢአታቸው ከተቆጠረ በኋላ፥ በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ ክፉ ሥራዎቻቸውም ሊከሷቸው በፊታቸው ይቆማሉ። |