Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ጥበብ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የደጋጐችና የክፉዎች ዕጣ ንጽጽር

1 የጻድቃን ነፍሶች በእግዚአብሔር እጅ ናቸው፤ ሥቃይ ከቶ አይነካቸውም፤

2 ለማያስተውሉ ዐይኖች የሞቱ መሰሉ፤ መለየታቸውም እንደ መከራ ተቆጠረ፤

3 ከእኛ መራቃቸውም እንደ መጥፊያቸው ታየ፤ እነርሱ ግን በሰላም ይኖራሉ።

4 የተቀጡ ሆነው በሰዎች ፊት ቢታዩም፥ ተስፋቸው ግን በዘላለማዊነት የለመለመ ነበር።

5 ጥቂት መከራ ተቀብለዋል፤ በረከታቸው ግን ታላቅ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ፈትኗቸው ለእርሱ የተገቡ ሆነው አግኝትዋቸዋልና።

6 ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን፥ እርሱም እነርሱን ፈተናቸው፤ እንደ ንጹሕ የተቃጠለ መሥዋዕትም ተቀበላቸው።

7 እርሱ በጐበኛቸውም ጊዜ እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ የእሳት ብልጭታ በቃርሚያ ውስጥ ቦግ እንደሚል እንዲሁ ይንቦገቦጋሉ።

8 በሀገሮች ላይ ይፈርዳሉ፥ በሕዝቦችም ላይ ይሾማሉ፤ ጌታም ለዘለዓለም ንጉሣቸው ይሆናል።

9 በእርሱ የሚያምኑ እውነትን ያውቃሉ፤ ታማኞች የሆኑም፥ ክብርና ምሕረት የቅዱሳን ፈንታ ነውና፥ እርሱም ስለ እነርሱ ይቆማልና፥ በፍቅር ከእርሱ ጋር ጸንተው ይኖራሉ።

10 ክፉዎች ግን ጻድቁን ንቀዋልና፥ ከእግዚአብሔርም ርቀዋልና፥ እንደ ሐሳባቸው የሚገባቸውን ቅጣት ይቀበላሉ።

11 በእርግጥም ጥበብንና ሥነ ሥርዓትን ያቃለሉ ጐስቋሎች ናቸው፤ ተስፋቸው ከንቱ፥ ልፋታቸው መና፥ የጥረታቸው ውጤትም ትርፍ አልባ ነው።

12 ሚስቶቻቸው ግዴለሾች፥ ልጆቻቸው ምግባረ ብልሹዎች፥ ዝርያዎቻቸው የተረገሙ ናቸው።


ስለ መኻንነት

13 ንጽሕት የሆነች፥ የኀጢአትንም አልጋ የማታውቅ መኻን ሴት፥ የተባረከች ነች፤ ነፍሶች በሚጐበኙበት ጊዜ ፍሬን ታገኛለች።

14 በእጆቹ ወንጀል ያልፈጸመ፥ በጌታም ላይ ክፉ ነገርን ያላሰበ ጃንደረባም የተባረከ ነው፤ ስለ ታማኝነቱ ልዩ ችሮታ ይደረግለታል፤ በጌታም ቤተ መቅደስ የእርሱ ድርሻ ከሁሉም የመረጠ ይሆናል።

15 ከልብ የመነጨ ጥረት ፍሬው ያስከብራል፤ የማስተዋልም ሥር አይበሰብስምና።

16 ነገር ግን የአመንዝራዎች ልጆች አያድጉም፤ የሕገ ወጥ አልጋ ፍሬዎችም ይጠፋሉ።

17 ረጅም ዕድሜ ቢያገኙ እንኳ ከንቱዎች ይሆናሉ፤ የሽምግልና ዘመናቸውም ያለ ክብር ያልፋል።

18 በአጭር የተቀጩ እንደሆነ ደግሞ፥ በፍርድ ቀን ተስፋም፥ መጽናናትንም አያገኙም፤

19 የክፉዎች ዘር መጨረሻው የከፋ ነውና።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች