Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ጥበብ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 የሚያቀርቡት የተሳሳተ ክርክርም ይህ ነው፥ ለራሳቸውም እንዲህ ይላሉ፦ ሕይወታችን አጭርና አሳዛኝ ናት፤ ፍጻሜያችን በደረሰ ጊዜ መዳኛ የለንም፤ ከሙታን ሀገር የተመለሰ ሰው አናውቅም።

2 እንደ አጋጣሚ ተወለድን፤ ከዚህም በኋላ እንዳልነበርን እንሆናለን፤ በአፍንጫችን ያለ ትንፋሻችን እንደ ጢስ ነውና፥ ሐሳባችንም ከልብ ምት የሚገኝ ብልጭታ ነው።

3 እርሱ ሲጠፋ ግን ሥጋችን አመድ ይሆናል፤ መንፈሳችን እንደ አየር ተበትኖ ይጠፋል።

4 ከጊዜ በኋላም ስማችን ይረሳል፤ የሠራነውንም የሚያስታውስ አይኖርም፤ ሕይወታችንም እንደ ደመና ነጠብጣብ የልፋል፤ የፀሐይ ጨረር እንዳባረረው፥ ሙቀቷ እንደገፈፈው ጉም ሟሙቶ ይቀራል።

5 ዕድሜያችን እንደ ጥላ ያልፋል፤ ከሞታችንም መመለሻ አይኖረንም፤ ማሸጊያው ተደርጓልና፥ ማንም ተመልሶ አይመጣም።

6 ስለዚህም ኑና የዛሬውን መልካም ነገር ሁሉ እንደሰትበት፥ የፍጥረትንም ምዕላት በወጣትነት ትኩሳት እንጠቀም።

7 ከወይን ጠጅና ከሽቶ የተመረጡትን እንውሰድ፤ በምንም የመፀው አበቦች አያምልጡን።

8 የፈኩትን ጽጌረዳዎች ከመጠውለጋቸው በፊት እንደ አክሊል እንቀዳጃቸው፤

9 ደስታችንን የማይጋራ በመካከላችን አይኑር፤ በሁሉም ቦታ የፈንጠዝያችንን ምልክት አንተው፤ ምክንያቱም ይህ ድርሻችን፥ ይህም ዕጣችን ነው!

10 ድኀና ትክክለኛ የሆነውን ሰው እንጨቁን፤ ስለ መበለቷም አንጨነቅ፤ ለሽበታም ሽማግሌዎች ክብር አንስጥ።

11 ደካማነት ራሱ እርባና ቢስነቱን ያረጋግጥልናልና፥ የመብታችን መለኪያው ኀይላችን ይሁን።

12 ትክክለኛ የሆነውን ሰው እናጥምደው፥ እርሱ ለእኛ ምቾት አይሰጠንም፤ ተግባራችንንም ይቃወማል፤ ከሕጉ ውጭ በፈጸምነው ኃጢአት ይጠላናል፤ ስለ ትምህርታችንም መተላለፍ ይከሰናል።

13 ስለ እግዚአብሔር አውቃለሁ ባይ ነው፥ ራሱንም የጌታ ልጅ ነኝ ይላል።

14 አስተሳሰባችንንም ነቃፊ ሆኖ አግኝተነዋል፤ እርሱን በማየት ብቻ መንፈሳችን ይሰበራል፤

15 ምክንያቱም የእርሱ አኗኗር ከሌሎች ሰዎች ጋር የማይመሳሰል፥ መንገዱም ፈጽሞ ልዩ ነው።

16 በእሱ ዘንድ እኛ የምንታየው እንደተናቀ ነገር ነው፤ ከርኩሰትም እንደሚርቅ ከመንገዳችን ይርቃል፤ የትክክለኛ ሰው ፍጻሜው የባረከ ነው ብሎ ያምናል፤ እግዚአብሔር አባቴ ነው በማለትም ይመካል።

17 እስቲ ንግግሩ ሁሉ እውነት ከሆነ እንመልከት፤ እርሱስ በሕይወቱ ፍጻሜ ምን እንደሚያጋጥመው እንፈትነው።

18 ትክክለኛው ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፥ እርሱ ይረዳዋል፤ ከጠላቶቹም እጅ ያወጣዋል።

19 በተንኰልና በስቃይ እንፈትነው፤ ደግነቱን እንመርምር፤ ትዕግስቱንም እንፈትነው።

20 አሳፋሪ ሞት እንፍረድበት፤ እግዚአብሔር ያድነዋልና፤ ወይም እርሱ ያድነኛል ብሏልና በማለት ክፉ ሰዎች ይሳለቃሉ።


የክፉዎች ስሕተት

21 እንግዲህ እነርሱ እንዲህ አሰቡ፤ በዚህም ሳቱ፤ ምክንያቱም ጥላቻቸው አሳውሯቸዋል።

22 እነርሱ የእግዚአብሔርን ምሥጢር አያውቁም፤ በቅድስና በሚገኘው ሽልማት ተስፋ አያደርጉም፤ ለንጹሐን ነፍሶች የሚሰጠውን ክብር አይቀበሉም።

23 እግዚአብሔር ሰዎችን የፈጠረው ዘላለማዊ እንዲሆኑ ነው፤ የፈጠራቸውም በእርሱ አምሳል ነው፤

24 ነገር ግን በዲያብሎስ ቅናት ሞት በዓለም ላይ ነገሠ፤ ከእርሱም ጋር የተወዳጁ ሁሉ የሚያገኙት ዋጋ ነው።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች