ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 በአንድ ቅዱስ ነቢይ ሥራቸው እንዲቃናላቸው አደረገች 2 የሰው እግር ባልደረሰበት ስፍራ፥ ድንኳኖቻቸውን ተከሉ። 3 ጠላቶቻቸውን በጽናት ተቋቋሙ ተቀናቃኞቻቸውንም አባረሩ። የመጀመሪያው ተቃርኖ የውሃው ተአምር 4 በተጠሙ ጊዜ ጥበብን ተጣሩ፤ ከአለታማው ገደል ውሃ፥ ከጽኑው ድንጊያ፥ የጥም ፈውስ ሰጠቻቸው። 5 ጠላቶቻቸውን ለመቅጣት ያገለገሉት ሁሉ፥ በመከራ ጊዜ እነርሱን ጠቀሟቸው፤ 6 ጠላቶቻቸው ግን ደምና ጭቃ ተለውሶ ያደፈረሰውን የማያቋርጥ የወንዝ ምንጭ ብቻ ነበራቸው፤ 7 እነርሱም ሕፃናትን ለመግደል ለወጡት አዋጅ የወረደባቸው ቅጣት ነው፤ ተስፋቸው በተሟጠጠ ወቅት ውሃ በብዛት ሰጠሻቸው፤ 8 አንዴ በደረሰባቸው የውሃ ጥም ጠላቶቻቸውን እንዴት ክፉኛ እንደቀጣሻቸው አሳየሻቸው። 9 የፍቅር እርምት ከሆነውና በራሳቸው ላይ ከደረሰው መከራ፥ በቁጣ የተፈረደባቸው ክፉዎች ሰዎች፥ ምን ያህል ስቃይ እንደ ደረሰባቸው ተገነዘቡ፤ 10 አባት እንደሚገሥጽ፥ አንቺም እንዲሁ የራስሽ የሆኑትን ፈተንሻቸው፤ ሌሎቹን ግን ጨካኝ ንጉሥ እንደሚሰጠው ፍርድ ዓይነት ቀጣሻቸው፤ 11 በዚህም ቅርብም ያሉት ሩቅ የመከራውን ገፈት እኩል ቀምሰውታል። 12 ድርብ ኀዘን ደርሶባቸዋል፤ ያለፈውንም ሰቆቃ በማሰብ አቀስተዋል። 13 ይደርስባቸው የነበረው ቅጣት፥ ሌሎቹን የሚጠቅም መሆኑን እንደተረዱ፥ የጌታ ሥራ መሆኑን ተገነዘቡ። 14 ቀደም ሲል ያዋረዱትንና ያላገጡበትን ሰው፥ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ አደነቁት፤ ምክንያቱም በጻድቃኑ ላይ ከደረሰው እጅግ የተለየ የውሃ ጥም ስለ ደረሰባቸው ነበር። እግዚአብሔር በግልፅ ላይ ያሳየው ትዕግስት 15 አእምሮ የሌላቸውንና የሚሳቡትን፥ የተጠሉትን ጢንዚዛዎች እስከማምለክ ባደረሳቸውና ከመንገድ ባወጣቸው ሞኝነታቸውና ክፉ ሐሳባቸው ምክንያት ልትቀጣቸው አእምሮ የሌላቸውን የእንስሳት መንጋ ላክህባቸው። 16 በዚህም የኃጢአት መሣሪያ የሆነ የቅጣትም መሣሪያ እንደሚሆን አስተማርኻቸው። 17 ዓለምን ቅርጽ አልባ ከሆነው ቁስ የፈጠረው ኃያሉ እጅህ እነርሱን ለመቅጣት፥ የድብ መንጋ፥ አስፈሪ አንበሶች፥ 18 ወይም ያልታወቁና እንግዳ የሆኑ፥ ቁጡና እሳት የሚተፉ፥ ወይም የሚከረፋ ጢስ የሚተፋ፥ ወይም ከአይኖቻቸው አስፈሪ ብልጭታን የሚወረውሩ፥ 19 በጭካኔያቸው ሊያጠፍዋቸው የሚችሉትን በአውሬዎች ብቻ ሳይሆን፥ በአስፈሪ መልካቸው ሊገድሏቸው የሚችሉትንም ቢሆን፥ በእነርሱ ላይ ማዝመት አንተን የሚሳንህ ሆኖ አይደለም። 20 ይሁን እንጂ ያለ አራዊቱም ቢሆን፥ በአንድ ትንፋሽ እንዲጠፉ ማድረግ አይቻል ነበርን። ተፈርዶባቸውና በኃይልህ ትንፋሽ ተበታትነው ሊቀሩ ይችሉ ነበር። የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት 21 ታላቁ ኃይልህ ሁልጊዜ በሥልጣንህ ሥር ነው፤ የክንደህን ኃይል ሊቋቋም የሚችልስ ይኖራልን 22 በምድር ላይ እንደሚወድቅ የማለዳ ጤዛ ጠብታ፥ መላው ዓለምም ላንተ እንደዚሁ በሚዛን ላይ እንደሚደረግ ኢምንት ክብደት ነው። 23 አንተ ግን ሁሉን ቻይ በመሆንህ፥ ምሕረትህ ለሰዎች ሁሉ ነው፤ ሰዎች ቢበድሉም ይጸጸቱ ዘንድ ታልፋቸዋለህ። 24 ፍጥረቶችህን ሁሉ ትወዳለህ፤ ከፍጡራንህ አንዱን ስንኳ አትጠላም፤ ምክንያቱም ብትጠላው ኖሮ አትፈጥረውምና። 25 ያለ አንተ ፈቃድ እንደምን ፍጡርህ ሊኖር ይችላል ባንተስ ባይጠራ ኖሮ እንደምን ይጠበቃል 26 የሕይወት ወዳጅ ጌታ ሆይ ሁሉም ያንተ ነውና ትጠብቀዋለህ። |