Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ጥበብ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ጥበብ ጥበብና የሰው ልጅ ዕጣ፥ ትክክለኛ ፍርድን ስለ መሻት

1 እናንተ የምድር ገዥዎች ሆይ፥ ጽድቅን አፍቅሩ፤ ጌታን በመልካምነት አስቡት፥ በቅን ልብም ፈልጉት፤

2 እርሱ በማይፈታተኑት ዘንድ ይገኛልና፤ በሚታመኑት ዘንድ ይገለጣልና።

3 ቀና ያልሆኑ ሐሳቦች ሕዝብን ከእግዚአብሔር ይለያያሉ፤ ኃይሉም ከተፈታተኗት ማስተዋል የጐደላቸውን ታሳፍራቸዋለች።

4 ጥበብ በአጥፊ ነፍስ፥ ለኃጢአት ባደረ ሥጋም አታድርምና።

5 ሰውን የሚያስተምር ቅዱስ መንፈስ አታላይነት ይሸሻል፤ ማስተዋል የጎደለውን አስተሳሰብ ይርቃል፤ ትክክለኛነት የጎደለውን አመል ባየ ጊዜም ያፈገፍጋልና።

6 ጥበብ የሰው ልጅ ወዳጅ የሆነች መንፈስ ናት፤ ክፉ ተናጋሪን ግን ከስድቡ ነጻ አታደርገውም፤ እግዚአብሔር ለውስጣዊ ማንነቱ ምስክር ነውና፥ ልቡን በጥልቀት ይመለከታል፤ የአንደበቱንም ቃል ይሰማል።

7 የጌታ መንፈስ ዓለሙን ስለ ሞላው፤ ሁሉንም ነገር የያዘ የሚባለውን ሁሉ ያውቃልና።

8 ስለዚህ ክፉ ቃል የሚናገር ከእርሱ አይሰወርም፤ ደም መላሿ ፍትሕም ለፍርድ ስትገለጥ አታልፈውም።

9 የክፉው ምክር ይመረመራል፤ የቃሉም ማስረጃ ለበደሉ መቀጣጫ ከጌታ ፊት ይቀርባል።

10 የቀናኢ ጆሮ ሁሉን ነገር ይሰማልና፥ የማጉረምረም ድምፅ እንኳን ሳይሰማ አያመልጥም።

11 እንግዲያውስ ከረብ የለሽ ማጉረምረም ተጠበቅ፤ ከሐሜትም አንደበትህን ከልክል፤ ምክንያቱም በምሥጢር የተነገረ ምላሽ ማሳየቱ፤ ውሸታምም አፍ ነፍስን ለሞት መስጠቱ አይቀርም።

12 በተሳሳተ አኗኗራችሁ በራሳችሁ ላይ ሞትን አትጋብዙ፤ በእጃችሁም ሥራ ጥፋትን አታምጡ።

13 እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረም፤ ሕያዋንንም በማጥፋት አይደሰትምና።

14 እርሱ እንዲኖሩ ሁሉንም ፈጠረ፤ የዓለም ፍጥረታት ጤነኞች ናቸው፤ በእነርሱም ዘንድ የጥፋት መርዝ አልነበረም፤ የሞትም ግዛት በምድር ላይ አልነበረም።

15 ትክክለኛነት ዘላለማዊ ነውና።


ሕይወት በክፉዎች ዐይን

16 ክፉዎች በቃላቸው፥ በሥራቸውም ሞትን ይጠሩታል፤ ወዳጅ አድርገውት ስለ እርሱ ራሳቸውን ያደክማሉ፤ የእርሱ ናቸውና ከእርሱ ጋር ይዋዋላሉ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች