ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)4 ጦቢያ 1 በዚያኑ ቀን ጦቢት በሜዶን በራጌስ ገባኤል ጋር ያሰቀመጠውን ብር አስታወሰ፥ 2 እንዲህ ሲልም አሰበ “እነሆ ልሙት ብዬ ለምኛለሁ፥ ከመሞቴ በፊት ልጄን ጦብያን ጠርቼ ስለ ብሩ ጉዳይ መንገር አለብኝ።” 3 ስለዚህ ልጁን ጦቢያን ጠራና እንዲህ አለው፦ “ስሞት በክብር ቅበረኝ፥ እናትህን አክበራት፥ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ አትለያት፥ ደስ የሚላትን ሁሉ አድርግላት፥ በምንም ነገር አታሳዝናት፤ 4 ልጄ ሆይ አንተ ገና በማሕፀንዋ ሳለህ ለአንተ ብላ የደረሰባትን መከረ አስታውስ፥ በሞተችም ጊዜ ከጎኔ በአንድ መቃብር ውስጥ ቅበራት። 5 ልጄ ሆይ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ለጌታ ታማኝ ሁን፥ ኃጢአትን ለመስራትና ሕጉን ለመተላለፍ አትፍቀድ፥ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ መልካም ሥራን ሥራ፥ መልካም ያልሆኑ መንገዶችን አትከተል፤ 6 በእውነተኛነት ከሠራህ በምትሠራው ሥራ ሁሉ ይሳካልሃል፥ ጽድቅን የሚያደርጉ ሁሉ ይቃናላቸዋል፤ 7 ከንብረትህ ሁሉ ምጽዋትን ስጥ፥ ፊትህን በድሆች ላይ አታዙር፥ እግዚአብሔርም ፊቱን ከአንተ አያዞርም። 8 ባለህ መጠን ምጽዋት ስጥ፥ ብዙ ካለህ ብዙ ስጥ፥ ጥቂት ካለህም ጥቂት ምጽዋት ለመስጠት አትፍራ፤ 9 ይህን በማድረግህ ለክፉ ቀን ትልቅ ሀብት ታከማቻለህ። 10 ምጽዋት ከሞት ያተርፋል፥ ወደ ጨለማ ከመግባትም ያድናልና። 11 በልዑሉ ፊት ለሚያደርጉት ሁሉ ምጽዋት መስጠት ከሁሉም የላቀ ስጦታ ነው። 12 ልጄ ሆይ ከዝሙት ተጠንቀቅ፥ ከሁሉ አስቀድመህ ከአባቶችህ ወገን የሆነች ሴት አግባ፥ እኛ የነቢያት ልጆች ነንና ከአባትህ ነገድ ያልሆነችውን ባዕድ ሴት አታግባ። ልጄ ሆይ ከጥንት ጀምሮ የነበሩትን አባቶቻችንን ኖኀን፥ አብርሃምን፥ ይስሐቅን፥ ያዕቆብን አስብ፤ ሁሉም ሚስት የወሰዱት ከወገኖቻቸው ነው፤ ስለዚህም በልጆቻቸውም የተባረኩ ሆኑ፤ ዘራቸውም ምድርን ይወርሳል። 13 አንተም ልጄ ሆይ ወንድሞችህን ውደድ፥ በወንድሞችህ፥ በሕዝብህ ልጆች ላይ አትታበይ፥ ከእነሱ መካከል ሚስት ምረጥ፤ ትዕቢት ጥፋትና ትልቅ ጭንቀት ያመጣልና፥ ስንፍናም ውድቀትንና ድህነትን ያመጣልና፥ የረኃብ እናት ስንፍና ናትና። 14 የሰሩልህን ሰዎች ደሞዝ በፍጥነት ከፈል እንጂ ለነገ አታሳድር። እግዚአብሔርን ካገለገልክ ዋጋህን ይከፍልሃል። ልጄ ሆይ በሥራህ ሁሉ ተጠንቀቅ፥ በጠባይህም ሁሉ ሥነ-ሥርዓት ያለህ ሁን። 15 አንተ የማትወደውን ነገር በማንም ላይ አታድርግ፤ እስክትሰክር ድረስ የወይን ጠጅ አትጠጣ፥ ስካር ከአንተ ጋር በመንገድህ አይሂድ። 16 ከምግብህ ለተራበ፥ ከልብስህም ለተራቆተ ስጥ፤ የተረፈህን በምጽዋት ስጥ፤ ምጽዋት ስትሰጥ ቅር ሳይልህ ስጥ። 17 በጻድቅ ቀብር ላይ በምግብና በወይን ለጋስ ሁን፤ ለኃጢአተኛ ግን አይሁን። 18 ከእያንዳንዱ ጠቢብ ሰው ምክርን ፈልግ፥ የሚጠቅም ምክርን አትናቅ። 19 ሁልጊዜ ጌታ እግዚአብሔርን አመስግን፤ መንገድህን ሁሉ እንዲያቃናልህ ጎዳናህንና ትልምህን ወደ ፍጻሜ እንዲያደርሰው ለምነው። ጥበብ የሁሉም ሕዝብ ሀብት አይደለምና፤ ነገር ግን መልካም ነገሮችን ጌታ ይሰጣል፤ እንደ ፈቃዱ ከፍ ያደርጋል ወይም ሙታን ወደሚኖሩበት ጥልቅ ይጥላል፥ አሁንም ልጄ ሆይ እነዚህን ምክሮች አስታውሳቸው፥ ከልብህም አይጥፉ። 20 አሁንም ልጄ ሆይ በሜዶን አገር በራጌስ በገብርያስ ልጅ በገባኤል ዘንድ አስር ታለንት ብር ማስቀመጤን ልነግርህ እወዳለሁ። 21 ልጄ ሆይ ድሆች በመሆናችን አትፍራ፤ እግዚአብሔርን ከፈራህና ከኃጢአት ሁሉ ከራቅክ፥ ጌታ አምላክህን ደስ የሚያሰኘው ነገር ሁሉ ካደረግህ ብዙ ሀብት አለህ።” |