ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጦቢት 1 ከዚህ በኋላ በልቤ አዝኜ፥ ተከዝሁ አለቀስሁም፤ ይህን የለቅሶ ጸሎት ጀመርሁ፦ 2 “ጌታ ሆይ አንተ እውነተኛ ነህ፥ ስራዎችህም ትክክለኛ ናቸው፥ በመንገዶችህም ሁሉ ጸጋና እውነት ናቸው፥ የዓለምም ፈራጅ አንተ ነህ። 3 ስለዚህ ጌታ ሆይ አስበኝ፥ ወደ እኔም ተመልከት፤ በኃጢአአቴ ምክንያት ወይም ሳላውቅ በአጠፋሁት ወይም አባቶቼ በአጠፉት አትቅጣኝ። 4 አንተን በድለናል ትእዛዞችህንም አፍርሰናልና፤ ለዝርፊያ፥ ለስደትና ለሞት፥ ተበትነን በምንኖርባቸው አገሮች ሁሉ ተንቀን መተረቻና ማላገጫ እንድንሆን አሳለፈህ ሰጥተኸናል። 5 በራሴና በአባቶቼ ኃጢአት ምክንያት እንዲህ በማድረግ ፍርዶችህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ ትዕዛዞችህን አልፈጸምንምና፥ በፊትህም በእውነት አልተራመድንምና። 6 አሁንም እንደ ፈቀድህ አድርገኝ፤ ከዚህች ምድር ተላቅቄ ዳግም አፈር ልሁን፥ ከመኖር መሞት ይሻለኛልና፥ ከንቱ ስድብን ተቋቁሜአልሁና፥ በታላቅ ኃዘንም ውስጥ ነኝ፤ ጌታ ሆይ ከዚህ መከራ እንድላቀቅ እዘዝ፥ ወደ ዘላለማዊ ቤቴም እንድሄድ ፍቀድ፤ ጌታ ሆይ ፊትህን ከኔ አትመልስ፤ በማያባራ ሰቆቃ ከተሞላ ሕይወት ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ፥ ከዚህ ወዲያ ስድቦችን መሸከም አልችልም።” 3 ሣራ 7 በዚያች ቀን በሜዶን በኤቅባጥና ከተማ የራጉኤል ልጅ ሣራ ከአባትዋ አገልጋዮች በአንዷ ተሰደበች። 8 ሰባት ጊዜ በጋብቻ ተሰጥታ ወንድ ከሴት ጋር እንደሚያደርገው ከእርሷ ጋር ከመተኛታቸው በፊት አስሞዴዩስ የተባለ ክፉ ጋኔን ባሎችዋን ይገላቸው ነበርና። ያች አገልጋይ እንዲህ አለቻት “ባሎችሽን የምትገድያቸው አንቺ ነሽ፥ ለሰባት ባሎች ተሰጥተሽ ነበር፥ ግን ከአንዱም ጋር አብረሽ አልኖርሽም፥ 9 ባሎችሽ ስለ ሞቱ እኛ የምንቀጣበት ምንም ምክንያት የለም፤ ሂጂና ተቀላቀያቸው፥ እኛም መቼም ቢሆን የአንቺን ልጅ አንይ።” 10 ያን ቀን አዘነች፥ ምርር ብላ አለቀሰች፥ ራስዋን ለመስቀል ወደ አባቷ ክፍል ገባች፤ ነገር ግን እንዲህ ብላ አሰበች፦ “አባቴን ‘የምትወዳትና ብቸኛዋ ልጅህ ከኀዘንዋ ክብደት የተነሣ እራስዋን ገደለች’ በማለት ይወቅሱታል፥ እኔም የአባቴን ሽምግልና ወደ ሞት የሚያፈጥን ኀዘን ማምጣት የለብኝም፤ ስለ ሆነም ራሴን ከመስቀል ይልቅ ዳግም የስድብ ቃላት ላለመስማት ከምኖር እንዲገድለኝ ጌታን እለምነዋለሁ።” 11 በዚያ ሰዓት ወደ መስኮቱ እጆችዋን ዘርግታ እንዲህ ስትል ጸለየች፦ “መሐሪ አምላክ ሆይ፥ የተባረክ ነህ፥ ስምህ ለዘለዓለም ብሩክ ይሁን፥ የሠራሃቸው ነገሮች በሙሉ ለዘለዓለም ይባርኩህ። 12 አሁንም ጌታ ፊቴን የምመልሰውና ዓይኔን የማቀናው ወደ አንተ ነው። 13 ከዚህ ዓለም እንድላቀቅና ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ስድብ እንዳልሰማ አድርገኝ። 14 ጌታ ሆይ በንጽሕና እንደቆየሁ ታውቃለህ፤ ማንም ወንድ ነክቶኝ አያውቅም፤ 15 በስደት ምድር ላይ የራሴንም ስም ሆነ የአባቴን ስም አላጎገፍኩም፤ ለአባቴም ብቸኛ ልጁ ነኝ፥ የሚወርሰው ሌላ ልጅ የለውም፥ እንዲሁም በአጠገቡ ወንድም የለውም፤ እራሴን የማቆይለት ዘመድም የለውም፤ እስከ አሁን ሰባት ባሎች ሞተውብኛል፥ ታዲያ ከዚህ በኋላ ለምን እኖራለሁ? ነፍሴን ለመው ካላስደሰትህ ግን ጌታ ሆይ እዘንልኝ፥ ከዚህ በኋላ ስሜ ሲጠፋ መስማት አልሻም።” 16 በዚህ ጊዜ የሁለቱ ጸሎት በእግዚአብሔር ክቡር (ሕልውና) ፊት ተቀባይነትን አገኘ። 17 ሁለቱንም እንዲፈውሳቸው ሩፋኤል ተላከ። ከጦቢት ዐይን የእግዚአብሔርን ብርሃን እንዲያይ ዓይኑ ላይ ያለውን ነጥብ ሊያጠፋለት፥ የራጉኤል ልጅ ሣራን ደግሞ ለጦቢት ልጅ ለጦብያ በሙሽርነት በመስጠት፥ ከአጋንንት ሁሉ ከከፋው ከአስሞዴዩስ ለማስጣል፥ በእርግጥም ከሁሉም አድናቂዎች ይልቅ የምትገባው ለጦብያ ነበርና፤ በተመሳሳይ ጊዜ ጦቢት ከግቢው አጥር ሲመለስ ሳለ የራጉኤል ልጅ ሣራ ከነበረችበት ክፍል ወደ ታች ደረጃውን በመውረድ ላይ ነበረች። |