ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)2 የጦቢት መታወር 1 በንጉሥ ኤሳራዶን ዘመን ወደ ቤቴ ተመለስሁ፥ ሚስቴን ሐናንና ልጄን ጦቢትንም መልሰው አመጡልኝ። የሳምንቶች በዓል በሆነው በጴንጤቆስጤ በዓላችን ቀን መልካም እራት ተዘጋጀልኝ፥ እኔም ለመብላት ተቀመጥሁ፤ 2 ምግቡ ቀረበልኝ፥ የተትረፈረፈ ምግብ እንደቀረበልኝ ባየሁ ጊዜ ልጄን ጦብያን እንዲህ አልሁት፦ “ልጄ ሆይ ሂድና ወደ ነነዌ ተማርከው ከመጡት ወንደሞቻችን መካከል የሆኑትንና ታማኝ ልቦና ያላቸውን ድኻ የሆኑትን ሰዎች ፈልግና ከማዕዴ እንዲካፈሉ አምጣቸው፤ ልጄ ሆይ እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ።” 3 ጦቢያ ከወንድሞቻችን መካከል ድኻ ለመፈለግ ሄደ፤ ግን ተመልሶ መጣና “አባቴ” አለኝ፤ እኔም “ምንድነው ልጄ?” አልሁት፤ እሱም “አባቴ ከወገኖቻችን አንዱ ተገድሎ በገበያ ተጥሎአል፤ በታነቀበት እዛው ወድቋል” አለኝ። 4 ምንም ሳልቀምስ፥ እራቴን ትቼ ተነስቼ ሄድሁ ሰውዬውን ከአደባባይ አነሳሁት፥ ፀሐይ ስትጠልቅ ለመቅበር ሬሳውን ከክፍሎቼ በአንዱ አኖርሁት። 5 ወደ ቤቴ ተመለስሁ፥ ታጠብሁና ምግቤን እያዘንሁ በላሁ። 6 ነቢዩ አሞፅ የቤተልን ሰዎች፦ “በዓላችሁ ወደ ኀዘን፥ መዝሙራችሁ ወደ ለቅሶ ይለወጣል” ያለውን አስታወስሁ። 7 እኔም አለቀስሁ። ፀሐይ በጠለቀች ጊዜ ሄድሁና ጉድጓድ ቆፈርሁ ቀበርሁትም። 8 ጐረቤቶቼ ሳቁብኝ እንዲህም አሉ፦ “ይህ ሰው ምንም አይፈራም፤ እንዲህ ያለ ሥራ በመስራቱ ሊገድሉት ፈልገው ሸሽቶ አምልጦ ነበር፤ አሁንም የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ይቀብራል።” 9 በዚያች ሌሊት ታጠብሁና ከግቢው አጥር ስር ተኛሁ፤ ሙቀት ስለ ነበረ ፊቴን አልሸፈንሁትም። 10 በግንቡ ላይ ድንቢጦች መኖራቸውን አላወቅሁም ነበር፤ ትኩስ ኩሳቸውም በዐይኖቼ ላይ ወደቀብኝና ነጭ ነጥብ ሆነ፤ ለመታከም ወደ ሐኪሞች ሄድሁ፥ ግን መድኃኒት ባደረጉልኝ ቍጥር ነጥቦቹ እየተጨመሩ ሄዱና ጭራሹን ታወርሁ። ለአራት ዓመታት ማየት አልቻልሁም፤ ዘመዶቼም በኔ ነገር በጣም ያዝኑ ነበር፤ አሂካር ወደ ኤሊማይስ እስከሄደበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመታት ተንከባከበኝ። 11 በዚያን ጊዜ ሚስቴ ሐና በሴቶች ሥራ ሱፍ በመፍተልና ልብስ አድርጋ በመሥራት ገንዘብ አገኘች። 12 የታዘዘችውን ሰርታ ታስረክባለች እነሱም ይከፍሏታል። በዲስትሮስ ሰባት አንድ ልብስ ሠርታ ጨረሰችና ለደንበኞቿ አስረከበች፤ እነሱም የሚገባትን ከከፈልዋት በኋላ በተጨማሪ ለእርድ አንድ የፍየል ጠቦት ሰጡዋት። 13 ፍየልዋ ወደ ቤቴ በመጣች ጊዜ መጮህ ጀመረች፤ እኔም ሚስቴን ጠራሁና “ይህች ፍየል ከየት መጣች? ምናልባት በስርቆት መጥታ ይሆናል፥ ወደ ባለቤቶችዋ መልሰሽ ውሰጃት፤ በስርቆት የመጣ ነገር መብላት አንችልምና” አልኳት። 14 እርሷም “ከደሞዜ በተጨማሪ የተሰጠችኝ ሥጦታ ናት” አለችኝ። እኔ ግን አላመንኳትም፥ ለባለቤቶችዋ እንድትመልስ ነገርኳት፥ በእስዋም በጣም አፈርሁ፤ እርሷም “አንተ ያደረግሃቸው ምጽዋቶች የት አሉ? መልካም ሥራዎችህስ ሁሉ የት አሉ? እነዚህን በጎ ተግባራት በመፈጸምህ ያገኘኸው ምን እንደሆነ ሁሉም ሰው ያውቃል።” ስትል መለሰች። |