Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽ​ሐፈ ጦቢት 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጦቢት መዝሙር መጨረሻ ነነዌ

1 የጦቢት መዝሙሮች ተፈጸሙ። ጦቢት በመቶ ዐሥራ ሁለት ዓመት ዕድሜው በሰላም ዐረፈ፥ በነነዌ ከተማም በክብር ተቀበረ።

2 የዓይኑን ብርሃን ሲያጣ ዕድሜው ስልሳ ሁለት ዓመት ነበር። ከተፈወሰ በኋላ በምቾት፥ ምጽዋት በመስጠት፥ ያለማቋረጥ እግዚአብሔርን በማመስገንና ትልቅነቱንም በማክበር ኖረ።

3 ሊሞትም በተቃረበ ጊዜ ልጁን ጦብያን ጠርቶ እነዚህን ትእዛዛት ሰጠው፤

4 “ልጄ ሆይ ልጆችህን ይዘህ በፍጥነት ወደ ሜዶን ሂድ፤ ምክንያቱም ነቢዩ ናሆም በነነዌ ላይ የተናረገውን የእግዚአብሔርን ቃል አምናለሁና፤ ሁሉ ነገር ይፈጸማል፤ የእግዚአብሔር ልዑካን፥ የእስራኤል ነብያት በአሦርና በነነዌ ላይ የተነበዩት ሁሉ ይፈጸማል። ከተናገሩት ቃል ሁሉ አንድም ነገር አይጐድልም፤ ሁሉም ነገር በጊዜው ይፈጸማል። ከአሦርና ከባቢሎን አገር ይልቅ በሜዶን አገር ከአደጋ ማምለጥ ይቻላል፥ ምክንያቱም እግዚአብሔር የተናረገው ሁሉ እንደሚሆንና እንደሚፈጸም አውቃለሁ፤ ይሆናልም። ከትንቢት አንድ ቃል እንኳ ሳይፈጸም የሚቀር የለም። በእስራኤል የሚኖሩ ወንድሞቻችን ከተቆጠሩ በኋለ ከውድ ሀገራቸው ይሰደዳሉ። የእስራኤል ድንበሮች በሙሉ በረሃ ይሆናሉ፤ ሰማርያና ኢየሩሳሌምም በረሃ ይሆናሉ፤ የእግዚአብሔር ቤትም ተቃጥሎ ለጥቂት ጊዜ ይፈራርሳል።

5 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንደገና ይራራላቸዋል፥ ወደ እስራኤል ምድርም ይመልሳቸዋል፤ እንደ በፊቱ ቆንጆ ባይሆንም ዘመኑ እስኪፈጸም ድረስ ቤቱን እንደገና ያንጻሉ፥ ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ከምርኮ ተመለሰው ይመጣሉ፥ ኢየሩሳሌምን ከነሙሉ ክብርዋ እንደገና ያንጽዋታል። የእግዚአብሔርም ቤት የእስራኤል ነቢያት እንደ ተነበዩት በውስጧ እንደገና ይታነጻል።

6 በምድር ያሉ ሰዎች ሁሉ ይለወጣሉ፥ ከልብም ጌታን ያከብራሉ፤ ሁሉም ወደ ስህተት የመሩአቸውን ጣዖቶቻቸውን ይተዋሉ፥

7 በጽድቅ የዘመናትን አምላክ ይባርካሉ። በእነዚህ ቀኖች የዳኑ እስራኤላውያን ከልባቸው እግዚአብሔርን ያስታውሱታል። ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ ይሰበሰባሉም፥ ከዛ በኋላም የእነሱ በምትሆን በአብርሃም ምድር ላይ ያለ ሥጋት ይኖራሉ። ከልባቸው እግዚአብሔርን የሚወዱ ደስ ይላቸዋል፤ ኃጢአትንና ክፋትን የሚያደርጉ ግን ከምድር ይጠፋሉ።

8 አሁንም ልጆቼ ሆይ ይህን ግዴታ እጥልባችሁአለሁ፤ ከልባችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር አድርጉ፤ ልጆቻችሁም ጽድቅን እንዲያደርጉ፥ ምጽዋትን እንዲያሰጡ፥ እግዚአብሔርን እንዲያስታውሱና ስሙን ሁልጊዜ ከልባቸውና በሙሉ ኃይላቸው እንዲባርኩ ግዴታ ጣሉባቸው።

9 ስለዚህ ልጄ ነነዌን ለቀህ ሂድ፥ እዚህ አትቆይ።

10 እናትህን እኔ አጠገብ እንደቀበርካት ቀኑ መቼም ይሁን መቼ በዚያኑ ቀን ሂድ፤ ክፋትና፥ ሸፍጥ ያለ ሃፍረት አሸንፎ በማይባት በዚች ከተማ ውስጥ አትቆይ። ልጄ ሆይ በአሳዳጊ አባቱ በአሂካር ላይ ናዳብ ያደረገውን ተመልከት፤ አሂካር በሕይወት እያለ ወደ ጉድጓድ እንዲገባ አልተደረገምን? እግዚአብሔር ግን የጭካኔ ሥራውን በተበዳዩ ዐይን ፊት እንዲከፍል አድርጎታል። ናዳብ አሂካርን ለመግደል ስለፈለገ ተቀጥቶ ወደ ዘለዓለም ጨለማ ወረደ፥ አሂካር ግን ወደ ብርሃን ወጣ፤ በደግ ሥራው ምክንያት አሂካር ናዳብ ካጠመደበት ከሞት ወጥመድ ወጣ፥ ናዳብ ግን ወደ እራሱ ወጥመድ ወደቀ።

11 ስለዚህ ልጆቼ ከምጽዋት ምን እንደ ሚገኝና ክፋት ወዴት እንደሚመራ አይታችሁአል፥ ሞትን ያመጣል፤ አሁን ግን ትንፋሽ አጠረኝ።” በአልጋው አስተኙት፤ ሞተ፥ በክብርም ተቀበረ።

12 ጦብያ እናቱ በሞተች ጊዜ ከአባቱ ጐን ቀበራት። ከዚህ በኋላ ከሚስቱና ከልጆቸ ጋር ወደ ሜዶን ሄደ፥ በኢቅባጥና ከአማቹ ከራጉኤል ጋር ተጠመቀ።

13 የሚስቱን አባትና እናት በእርጅናቸው ጊዜ በክብር ያዛቸው። ኋላም በሜዶን በኢቅባጥና ከተማ ቀበራቸው። ጦብያ ከአባቱ ከጦቢት ሀብት በተጨማሪ የራጉኤልን ሀብት ወረሰ።

14 ተከብሮ፥ እድሜው መቶ ዐሥራ ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ ሞተ።

15 ከመሞቱ በፊት የነነዌን መጥፋት አየ፥ የነነዌ ሰዎች በሜዶን ንጉሥ በሳያቅሳሬስ ተማርከው ወደ ሜዶን ሲመጡ አየ። በነነዌያውያን እና በአሶራውያን ላይ ስላወረደው ቅጣት ሁሉ እግዚአብሔርን ባረከ። ከመሞቱ በፊት በነነዌ በደረሰው ጥፋት ተደሰተ፥ ጌታ እግዚአብሔርንም ለዘለዓለም ዓለም ባረከ። አሜን።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች