ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ራእይ 1 የሰርጉ በዓል በተፈጸመ ጊዜ ጦቢት ልጁን ጦብያን ጠርቶ “ልጄ አብሮህ ለሄደው ሰው ደሞዙን ክፈለው፥ ሌላም ነገር ጨምርለት” አለው። 2 ጦብያም እንዲህ አለው “አባቴ ምን ያህል ልስጠው? ከእኔ ጋር አብሮ ይዞት ከመጣው ገንዘብ ሁሉ ግማሹን ብሰጠውም እንኳን ምንም አይጐዳኝም፥ 3 እሱ እኔን በደህና መልሶ አመጣኝ፥ ሚስቴን አዳነ፥ ገንዘቡን አመጣ፥ አንተንም ፈወሰ፥ ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ ታዲያ ምን ያህል ልስጠው?” 4 ጦቢትም “ልጄ ካመጣው ሁሉ ግማሹን መውሰድ ይገባዋል” አለው። 5 ጦብያም ጠራውና “ካመጣኸው ገንዘብ ሁሉ ግማሹን ውሰድና በሰላም ሂድ።” አለው። 6 በዚያን ጊዜ ሩፋኤል ሁለቱንም ለብቻቸው ገለል አደረገና እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔርን ባርኩ፥ ያደረገላችሁንም በሕያዋን ሁሉ ፊት ምስጋናውን አውሩ፥ ስሙንም ባርኩ፥ አመስግኑም። የእግዚአብሔርን ሥራ ለሰዎች ሁሉ በሚገባ አስታወቁ፥ እሱን ከማመስገን ቸል አትበሉ። 7 የንጉሥን ምሥጢር ደብቆ መያዝ መልካም ነው፥ የእግዚአብሔርን ሥራዎች ግን መግለጥና መናገር ያስፈልጋል፥ መልካምን አድርጉ፥ ክፉም አይደርስባችሁም። 8 ጸሎት ከጾም ጋር፥ ምጽዋትም ከጽድቅ ጋር፥ በተንኰል ከመበልፀግ የበለጡ ናቸው። ወርቅን ከመሰብሰብ ምጽዋት መስጠት ይበልጣል። 9 ምጽዋት ከሞት ያድናል፥ ከሁሉም ዓይነት ኃጢአት ያነጻል። ምጽዋት የሚሰጡ ሙሉ ሕይወት ይኖራቸዋል። 10 ኃጢአትንና ክፋትን የሚያደርጉ የገዛ ራሳቸው ጠላቶች ናቸው። 11 አሁን እውነቱን ሁሉ እነግራችኋለሁ፥ ምንም አልደብቃችሁም፥ የንጉሥን ምስጢር ደብቆ መያዝ፥ የእግዚአብሔርን ሥራዎች ግን በግልጽ መናገር መልካም ነው ብዬ ነግሬአችኋለሁ። 12 አንተና ሣራ በጸሎት ላይ በነበራችሁ ጊዜ ጸሎታችሁን በጌታ ክብር ፊት ያቀረብሁና ያነበብሁ እኔ ነኝ፥ አንተም የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ስትቀብር እንዲሁ። 13 ምንም ሳታመነታ የሞተውን ሰው ሬሳ ለመቅበር ከማዕድ ትተህ በተነሣህጊዜ በዚያን ሰዓት እንድፈትንህ ተላክሁ። 14 በተመሳሳይ ሰዓትም እግዚአብሔር አንተንና የልጅህን ሚስት ሣራን እንድፈውስ ላከኝ፤ 15 በጌታ ክብር ፊት ከሚገቡትና ከሚቆሙት፥ ከሰባቱ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ።” 16 ሁለቱም በጣም ደንግጠው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ በመሬት ላይ በግንባራቸው ተደፉ። 17 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፥ ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን፥ ዘለዓለም እግዚአብሔርን ባርኩት፤ 18 ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፥ ወደ እናንተ የመጣሁት በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ በራሴ አይደለም፤ በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ መባረክ የሚገባችሁ እሱን ነው፥ ማመስገን የሚገባችሁ እሱን ነው። 19 ስበላ ያያችሁኝ ይመስላችኋል፥ ያ ግን እይታ ብቻ ነው። 20 አሁምን ከምድር ተነሱ እግዚአብሔርንም እወቁ። ወደ ላከኝ ወደ እርሱ እወጣለሁ። የሆነውን ነገር ሁሉ ጻፉት።” ወደ ላይም ወጣ። 21 ከዚያም በኋላ ተነሱ፥ ሊያዩትም አልቻሉም። እግዚአብሔርን በዝማሬ አመሰገኑ፥ ታላላቅ ነገሮችን ስላደረገላቸውና የእግዚአብሔር መልአክ ስለታያቸው አመሰገኑት። |