Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽ​ሐፈ ጦቢት 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጦቢት ዐይን በራ

1 ከነነዌ ትይዩ ወደምትገኘው ወደ ካሠሪን ከተማ በደረሱ ጊዜ

2 ሩፋኤል ጦብያን “አባትህን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደተውነው ታውቃለህ፤

3 ስለዚህ እኛ ከሚስትህ በፊት ቀድመን እንሂድና እነሱ እስኪመጡ ድረስ ቤቱን እናዘጋጅ” አለው።

4 ሁለቱም አብረው ሄዱ፤ ሩፋኤል ጦብያን “ሐሞቱን በእጅህ ያዘው” አለው፤ ውሻውም ተከተላቸው።

5 ሐና ልጇ የሚመጣበትን መንገድ እየተመለከተች ተቀምጣ ነበር።

6 ልጇ ሲመጣ አየችና አባቱን “ያውልህ ልጅህ አብሮት ከሄደው ሰው ጋር እየመጣ ነው” አለችው።

7 ሩፋኤል ጦብያን ወደ አባቱ ከመድረሱ በፊት እንዲህ አለው “የአባትህ ዐይኖች እንደሚከፈቱ አውቃለሁ፤

8 የዓሣውን ሐሞት በዐይኖቹ ላይ ቀባው፥ መድኀኒቱ የዐይኖቹን ነጥቦች እንዲወድቁ ያደርገዋል፥ የአባትህ ብርሃንን ያያል እንጂ ከአሁን በኋላ ዕውር አይሆንም።”

9 ሐና ሮጣ በልጇ አንገት ላይ ተጠምጥማ “ልጄ አየሁህ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ግድ የለም ልሙት።” አለችው፤ ታለቅስም ጀመር።

10 ጦቢት ተነስቶ እየተደነቃቀፈ ከግቢው በር ወጣ። ጦብያም ወደ እርሱ ሄደ፥

11 የዓሣውን ሐሞት በእጁ እንደ ያዘ፥ ጠበቅ አድርጎ ይዞ በዐይኖቹ ላይ እፍ አለበትና “በርታ አባቴ” አለው። በዚህም ዓይነት መድኃኒቱን አደረገለት። ለጥቂትም ጊዜ በዛ ተወው።

12 ከዛ በኋላ በሁለት እጆቹ ከዐይኖቹ ጥግ ላይ ስስ ቆዳ ቀረፈለት።

13 በዚያን ጊዜ አባቱ በአንገቱ ላይ ተጠመጠመ፥

14 አለቀሰ። “የዓይኔ ብርሃን ልጄ አየሁህ” አለ። ቀጥሎም እንዲህ አለ “እግዚአብሔር ይባረክ፤ ታላቅ ስሙ ይባረክ፤ ቅዱሳን መላእክት ሁሉ ይባረኩ፤ ታላቅ ስሙ ለዘለዓለም የተባረከ ይሁን፤ መላእክት ሁሉ ለዘለዓለም የተመሰገኑ ይሁኑ፤

15 በመከራ ቀጥቶኝ ነበር፥ ምሕረት አደርገልኝ፥ አሁን ልጄን ጦብያን አየሁት።” ጦብያ ደስ ብሎት በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤት ገባ። ሁሉንም ነገር ማለትም መንገዱ እንዴት እንደ ተቃናለት፥ ገንዘቡንም ተቀብሎ እንደመጣ፥ የራጉኤልን ልጅ ሣራን እንዴት እንደአገባት በነነዌ ከተማ አጠገብ እንደደረሰችና በቅርብ እንደምትምጣ ለአባቱ ተረከለት።

16 ጦቢት ደስ ብሎት እግዚአብሔርን እያመሰገነ የልጁን ሚስት ለመቀበል ወደ ነነዌ በር ወጣ። የነነዌ ሰዎች ጦቢትን ማንም ሳይመራው ሲራመድና ሲዘዋዋር ባዩት ጊዜ ተደነቁ።

17 ጦቢትም እግዚአብሔር እንደራራለትና ዐይኖቹን እንደ ከፈተለት በእነሱ ፊት ይናገር ነበር። በዚያን ጊዜ ጦቢት ከልጁ ከጦብያ ሚስት ከሣራ ጋር ተገናኘ፥ እንዲህም ብሎ ባረካት “ልጄ እንኳን ደኀና መጣሽ፥ ልጄ ወደኛ ያመጣሽ አምላክሽ የተባረከ ይሁን፥ አባትሽና እናትሽ የተባረኩ ይሁኑ፥ የእኔ ልጅ ጦብያም የተባረከ ይሁን፥ አንቺም ልጄ የተባረክሽ ሁኚ፥ በደስታና በበረከት ቤትሽ እንኳን በደኀና መጣሽ፥ ግቢ ልጄ።” በዚያን ቀን በነነዌ በሚኖሩ አይሁዳውያን መካከል ደስታ ሆነ።

18 የጦቢት የአጎቱ ልጆች አሂካርና ናዳብም የጦቢትን ደስታ ለመጋራት መጡ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች