ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 እስከዚያ ድረስ ጦቢት ለመሄድና ለመመለስ ምን ያህል ቀኖች እንደሚያስፍልጉ ቀኖቹን በየቀኑ ይቆጥር ነበር። ቀኖቹ ሁሉ አለፉ፥ ልጁ ግን ገና አልተመለሰም ነበር። 2 እሱም “ምናልባት ልጄን እዚያ ይዘውት ይሆን? ምናልባት ጋባኤል ሞቶ ገንዘቡን የሚሰጠው ሰው አጥቶ ይሆን?” ብሎ አሰበ፤ 3 መጨነቅም ጀመረ። 4 ሚስቱ ሐና “ልጄ ሞቷል፥ በሕያዋን መካከልም የለም” ትል ጀመር። ስለ ልጇ እንዲህ እያለች ማልቀስና ማዘን ጀመረች፥ 5 “ወዮልኝ ልጄ፥ የዓይኔ ብርሃን፥ አንተን መላክ አልነበረብኝም።” 6 ጦቢትም እንዲህ ብሎ መለሰላት “እኀቴ ዝም በይ አትጨነቂ፤ እሱ ደህና ነው፤ እዚያ አንድ የሚያዘገይ ነገር አጋጥሞአቸው፤ አብሮት የሄደው የታመነ ሰው ነው፤ ከወንድሞቻችን ወገን ነው፤ እኀቴ ስለ እሱ አትዘኚ፤ 7 አሁን በቅርቡ ይመጣል።” እርሷ ግን “ተወኝ፥ እኔን ማታለል ይቅርብህ፥ ሞቷል” በማለት መሰለችለት። ዓይኗን እንጂ ማንንም ስለማታምን ልጇ የሄደበትን መንገድ ለመመልከት በየቀኑ ፈጥና ትወጣ ነበር። ፀሃይ ስትጠልቅ ወደ ቤትዋ ትመለስ ነበር፤ ሌሊቱን ሙሉ እያዘነችና እያለቀሰች ታድር ነበር፥ እንቅፍል አይወስዳትም ነበር። ራጉኤል ለልጁ ሲል ምሎ የወሰናቸው ዐሥራ አራት የሰርግ ቀኖች እንዳልፉ፥ ጦብያ ወደ እርሱ ሄደና እንዲህ አለው “እንድሄድ ፍቀድልኝ አባትና እናቴ ከእንግዲህ ወዲህ አናየውም ብለው ተስፋ ቆርጠው ይሆናል፤ ስለዚህ እባክህ አባቴ እንድሄድ ፍቀድልኝ፥ ወደ አባቴ ቤት ልመለስ፥ በምን ሁኔታ ላይ እንደተውኩት አስቀድሜ ነግሬሃለሁ።” 8 ራጉኤልም ጦብያን “ቆይ ልጄ ከእኔ ጋር ቆይ፥ ወደ አባትህ ወደ ጦቢት ያንተን ሁኔታ እንዲነግሩት መልዕክተኞችን እልካለሁ” አለው። 9 ጦብያም ግን “አይሆንም፥ ወደ አባቴ ለመመለስ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ” አለው። 10 ራጉኤል ወዲያውኑ ሚስቱን ሣራን ለጦብያ አስረክበው፥ በተጨማሪም የንብረቱ ሁሉ ግማሽ፥ ወንድና ሴት አገልጋዮች፥ በሬዎችና በጐች፥ አህዮችና ግመሎች፥ ልብሶች፥ ገንዘብና የቤት ዕቃዎች ሰጠው። 11 በደስታ ሸኛቸው፤ ጦብያን ሲሰናበተው እንዲህ አለው “ልጄ ደኀና ሁን፥ መልካም ጉዞ፥ የሰማዩ ጌታ አንተንና ሚስትህ ሣራን ሞገስ ይሁናችሁ፥ ከመሞቴ በፊት ልጆቻችሁን ለማየት ያብቃኝ።” 12 ልጁን ሣራንም እንዲህ አላት “አማቾችሽን አክብሪያቸው፥ ምክንያቱም ከእንግዲህ ወዲህ ከወለዱሽ ይልቅ ወላጆች የሚሆኑሽ እነሱ ናቸውና፤ በሰላም ሂጂ ልጄ፥ በሕይወቴ ሳለሁ ስለ አንቺ መልካም ወሬ ብቻ ያሰማኝ።” ተሰናበታቸውና ሸኛቸው። ኤድናም በተራዋ ጦብያን እንዲህ አለችው “እጅግ የተወደድህ ልጄና ወንድሜ፥ ጌታ በደኀና ይመልስህ፥ እኔም ከመሞቴ በፊት ያንተንና የልጄን የሣራን ልጆች ለማየት ያብቃኝ፤ በጌታ ፊት ልጄን እንድትጠብቃት ለአንተ አስረክባታለሁ፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምንጊዜም አታሣዝናት፤ በሰላም ሂዱ ልጄ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እኔ እናትህ ነኝ፥ ሣራ ደግም እኀትህ ናት። ሁላችንም በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በደስታ ያኑረን።” ከዚህ በኋላ ሁለቱንም ሳመቻቸውና በደስታ ሸኘቻቸው። 13 ጦብያ በደስታና በሰላም ከራጉኤል ቤት ወጣ፤ በደስታው የሰማይና የምድር፥ የሁሉም ንጉሥ የሆነውን ጌታ መንገዱን ስላቃናለት አመሰገነ። ራጉኤልንና ሚስቱን ኤድናን እንዲህ ሲል ባረካቸው “በቀሪው ዘመኔ ሁሉ እናንተን እንዳከብር በጌታ ታዝዣለሁ።” |