ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የቶብኤል ልጅ፥ የአናኒኤል ልጅ፥ የአዱኤል ልጅ፥ የጋባኤል ልጅ፥ የሩፋኤል ልጅ፥ የራጉኤል ልጅ፥ የአሲኤል ዘር፥ የኔፍታሊም ወገን የሆነው ጦቢት የቃሉ መፅሐፍ ይህ ነው። 2 እሱም በአሦር ንጉሥ በሸልማንሰር ዘመን፥ ከላይኛው ገሊላ ክፍል ከቄዴሽ ኔፍታሊም በስተ ደቡብ፥ ከአሼር ወደ ምዕራብና ከፎጎር በስተ ሰሜን ከምትገኘው ከቲስቤ በምርኮ ተወስዶ የነበረው ነው። ስደተኛው ጦቢት 3 እኔ ጦቢት በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእውነት መንገድና በጽድቅ ሄድሁ፤ ወደ አሦር አገር ወደ ነነዌ ከኔ ጋር ተማርከው ለመጡት ወንድሞቼና ወገኖቼ ብዙ መጽውቻለሁ። 4 በአገሬ እስራኤል ምድር በነበርኩበት ጊዜና ገና ወጣት ሳለሁ፥ የአባቶቼ የናፍታሊ ወገኖች በሙሉ የዳዊትን ቤትና ኢየሩሳሌምን ጥለው ሄዱ። ይህች ከተማ ከእስራኤል ነገዶች በሙሉ ተመርጣ፥ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆነው በቤተ መቅደሱ፥ የእስራኤል ነገዶች መሥዋዕት እንዲያቀርቡባት፥ ለትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ተቀድሳና ታንፃ ነበር። 5 ዘመዶቼና የአባቶቼ የናፍታሊ ወገኖች ሁሉ፥ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በገሊላ ተራራዎች ላይ በዳን ላቆመው ጥጃ መሥዋዕት አቀረቡ። 6 ለመላው እስራኤል በተሰጠው ለዘለዓለም ጸንቶ በሚኖረው ትእዛዝ መሠረት ለበዓላት ብዙ ጊዜ ብቻዬን ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ነበር። ካመረትሁት ሁሉ የመጀመሪያውን አሥራት ከከብቶቼም በመጀመሪያ የተወለደውን፤ ከበጐቼም በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጉር ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድና በቤተ መቅደስ 7 እነዚህን ለካህናቱ ለአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሰጥ ነበር። የወይን፥ የእህል፥ የወይራ፥ የሮማንና ሌሎችም ፍሬዎች አስራት በኢየሩሳሌም ለሚያገለግሉ ሌዋውያን እሰጥ ነበር። መሬት በማይታረስበት በሰባተኛው ዓመት ካልሆነ በቀር በየዓመቱ ሁለተኛውን አሥራት በጥሬ ገንዘብ ለውጬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድና እከፍል ነበር። 8 ሶስተኛውን አሥራት ለሙት ልጆች፥ ለመበለቶችና ከእሥራኤል ልጆች ጋር ለሚኖሩ እንግዶች እሰጥ ነበር፤ በየሶስት ዓመቱ እንደ ስጦታ እሰጣቸው ነበር፤ ስንበላም በሙሴ ሕግ ለተደነገገውና ለአያታችን ለአናኒኤል እናት ምክር እንታዘዝ ነበር፥ እኔ አባቴ ሞቶብኝ የሙት ልጅ ነበርሁና። 9 ለአቅመ አዳም በደረስሁ ጊዜም ዘመዳችን የሆነችውን ሐናን አገባሁ፤ በእርሷም ጦብያ ብዬ የጠራሁትን ወንድ ልጅ አገኘሁ። 10 ግዞት ወደ አሦር በመጣ ጊዜ፥ እኔም ተወሰድሁ ወደ ነነዌም መጣሁ። ወንድሞቼና ወገኖቼ ሁሉ የአረማውያንን ምግብ በሉ፤ 11 እኔ ግን የአረማውያንን ምግብ ከመብላት እራሴን ገታሁ። 12 ምክንያቱም በሙሉ ልቤ እግዚአብሔርን አስብ ነበር፤ 13 ልዑል አምላክ በንጉሡ በሸልማንሰር ዘንድ ሞገስንና ባለሟልነትን ሰጠኝ፥ ንጉሡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አቅራቢ ሆንኩኝ። 14 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አስፈላጊውን ለመግዛት ወደ ምድያም እመላለስ ነበር። ምድያም በተባለው ቦታ ሳለሁ ለገብርያስ ወንድም ለገባኤል የሚመዝን ብር በአደራነት እንዲያስቀምጥልኝ በከረጢቶች አድርጌ ሰጠሁት። 15 ሸልማንሰር በሞተ ጊዜና በቦታውም ልጁ ሰናክሬም በተተካ ጊዜ ግን ወደ ምድያም የሚወስደው መንገድ ተዘጋ፥ እኔም ወደዚያ ለመሄድ አልቻልሁም። 16 በሸልማንሰር ጊዜ ለወገኖቼ ብዙ ጊዜ እመጸውት ነበር። 17 ምግቤን ለተራቡ፥ ልብሶችን ደግሞ ለታረዙ እሰጥ ነበር። የወገኖቼ ሬሳ ከነነዌ ቅጥር ውጪ ተጥሎ ባየሁ ጊዜ እቀብር ነበር። 18 በሰናክሬም የተገደሉትን ሁሉ ጭምር እቀብር ነበር። ሰናክሬም በተሳደበው ስድብ ምክንያት የሰማይ ንጉሥ ቀጥቶት ከይሁዳ ሸሽቶ በመጣ ጊዜ ተበሳጭቶ ነበርና ብዙ እስራኤላውያንን ገደለ፤ እሱ የገደላቸውን ሰዎች ሬሳ እየሰረቅሁ እቀብር ነበር፤ ሬሳቸውንም ሲፈልገው አያገኘውም ነበር። 19 ከነነዌ ሰዎች አንዱ ወደ ንጉሡ ሄዶ የሰዎቹን ሬሳ በምሥጢር የቀበርሁ እኔ መሆኔን ተናገረ፤ ንጉሡ ስለ እኔ ማወቁንና እኔም ለመገደል እየተፈለግሁ መሆኑን ስገነዘብ ፈራሁና ሸሸሁ። 20 ያለኝን ንብረት ሁሉ ተይዞ ነበር፤ ሁሉም በግምጃ ቤቱ ተወርሰው ነበር፤ ከሚስቴ ሐናንና ከልጄ ጦብያ በስተቀር ምንም አልቀረም። 21 ይህ ከሆነ አርባ ቀን ሳይሞላው ሁለቱ ልጆቹ ንጉሡን ገደሉት፥ ከዛም ወደ አራራት ተራራዎች ሸሹ፤ ልጁ ኤሳራዶን ተተካ። የወንድሜ የአናኤል ልጅ አሂካር የመንግሥት ገንዘብ አስተዳዳሪና የአስተዳደሩ ዋና ሆኖ ተሾመ። 22 ከዚህ በኋላ አሂካር አማለደኝና ወደ ነነዌ እንድመለስ ተፈቀደልኝ። በአሦር ንጉሥ በሰናክሬም ጊዜ አሂካር የወይን ጠጅ ቀጂዎች አለቃ፥ የመንግሥት ማኀተም ጠባቂ፥ የገንዘብ ቤቱ አስተዳዳሪና ነበር። ንጉሡ ኤሳራዶንም በዚህ በሥራው ላይ በድጋሚ ሾመው። እርሱም ዘመዴ የወንድሜ ልጅ ነበር። |