Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 50 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሊቀ ካህኑ ስምዖን

1 በሕይወት ዘመኑ ቤተ መቅደሱን ያደሰ፥ የእግዚአብሔርን ቤት የገነባ፥ የኦንያስ ልጅ ሊቀ ካህናት ስምዖን ነበር።

2 መሠረቱን በእጥፍ ጥልቀት ገነባ፥ በቤተ መቅደሱ አጠገብ የሚገኙትን ከፍተኛ መደገፊያዎች ሠራ።

3 ኩሬው የተቆፈረው በእርሱ ጊዜ ነው፥ እርሱም እንደ ባሕር የገዘፈ የውሃ ማጠራቀሚያ ነው።

4 ሕዝቡን ከጥፋት ለማዳን በማሰቡ፥ ከተማዋንም ከከበባ ለመከላከል ምሽግ ሠራ

5 መገረጃውን ገልጦ ብቅ ሲልና በሕዝቡ ተከቦ ሲራመድ፥ እንደምን ያስደስት ነበር!

6 በደመና መካከል እንደምትወጣው የንጋት ኮከብ፥ እንደ ሙሉ ጨረቃ፥

7 በልዑል እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደምታበራው ፀሐይ፥

8 እንደ ፀደይ ወራት ጽጌረዳ፥ በውሃ ዳር እንደበቀለች ነጭ አበባ፥ በበጋ እንደሚታየው የዕጣን ዛፍ ቅርንጫፍ፥

9 በጥናው ላይ እንዳለው እሳትና ዕጣን፥ በከበረ ደንጊያ እንደተለበጠ ግዙፍ የወርቅ ሳህን፥

10 ፍሬው እንደከበደው የወይራ ዛፍ፥ ደመናዎችን ለመንካት እንደሚምዘገዘግ የጥድ ዛፍ፥ የደስ ደስ ነበረው።

11 የክብር ቀሚሱን ሲለብስና ጌጣጌጦቹን ሲያደርግ፥ ወደተቀደሰው የመሠዊያ ሲወጣና አካባቢውን ግርማ ሞገሱ ሲያደምቀው፥

12 ከመሠዊያው ምድጃ አጠገብ ቆሞ፥ ከካህናቱ እጅ ድርሻዎቹን ሲቀበል፥ የሊባኖስ ዝግባ በቅጠሉ እንደሚሸፈን፥ በዘንባባ ግንዶች እንደተከበበ ሁሉ፥ እርሱንም ወንድሞቹ ከበውት አክሊል ይሆኑታል።

13 የአሮን ልጆች ሁሉ፥ በክብር አጊጠው፥ ለጌታ የሚቀርበውን መሥዋዕት፥ በእጆቻቸው እንደ ያዙ በመላው እስራኤል ጉባኤ ፊት ይቀርባሉ።

14 እርሱም በበኩሉ በመሠዊያው ሥርዓተ አምልኮን ይፈጽማል፤ ለኃያሉና ለታላቁ አምላክ መሥዋዕቶቹን በክብር ያቀርባል።

15 ጽዋውን ያነሣል፥ የወይኑንም ጭማቂ በዙሪያው ያፈሳል፥ በመሠዊያው ግርጌ ይረጫል፤ መዓዛውም የዓለምን ንጉሥ ልዑል እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል።

16 ያኔ የአሮን ልጆች ይጮሃሉ፥ የብረት ጡሩምባቸውን ይነፋሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት አስታዋሽ የሚሆን ከፍተኛ ድምፅ ይሰማል።

17 ሕዝቡም ሁሉ በፍጥነት በፊታቸው መሬት ላይ ይደፋሉ፤ ለጌታቸው ለኃያሉ ልዑል እግዚአብሔር ያላቸውንም ፍቅር ይገልጻሉ፤

18 መዘምራኑም የምስጋና መዝሙር ያሰማሉ፥ የሁሉም ድምፅ ዜማው ጣፋጭ ነው።

19 የጌታ ሥርዓተ ጸሎትና ሥርዓተ አምልኮው እስኪፈጸም ድረስ፥ በመሐሪው አምላክ ፊት ይጸለያሉ፥ ታላቁን አምላክ ይማፀናሉ፤

20 እርሱም ወደ ታች ወርዶ፥ በመላው እሥራኤል ጉባኤ ላይ እጆቹን ያነሣል፥ ስሙን ለመጥራት ታድሏልና የጌታ ቡራኬም በአንደበቱ ይናገራል።

21 ሕዝቡም የልዑል እግዚአብሔርን በረከት ለመቀበል በሁለተኛ ጊዜ ይሰግዳሉ።


ልመና

22 በየትኛውም ቦታ፥ የታላላቅ ሥራዎችን ፈጣሪ፥ ከእናታችን ማሕፀን ጀምሮ ሕይወታችንን የታደገውን፥ በምሕረቱም የሚጠብቀንን፥ የሁሉንም አምላክ አመስግኑ።

23 ደስተኛ ልብ ይስጠን፤ በዘመናችን ደስታ፥ ለእስራኤል ደግሞ ዘላለማዊ ሰላምን ይስጥ።

24 ምሕረቱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ይሁን፥ በዘመናችን ደኀንነትን ይስጠን።


አኃዛዊ ምሳሌ

25 ነፍሴ የምትጠላቸው ሁለት ሕዝቦች አሉ፤ ሦስተኛው ፈጽሞ ሕዝብ አይደለም፥

26 የሴኤር ተራራ ሠፋሪዎች፥ ፍልስጥኤማውያንና በሴኬም የሚኖረው ማስተዋል የጐደለው ሕዝብ ነው።


መደምደሚያ

27 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረበው፥ የዕውቀትና የጥበብ ትምህርት ነው።

28 ይህ ከልብ የመነጨ የጥበብ ዝናብ የፈሰሰው፥ ከኢየሩሳሌም ሲራክ አልዓዛር ልጅ ከኢየሱስ ነው። በልቡ የሚያሳድራቸውም ሰው ጥበበኛ ይሆናል።

29 በሥራ የሚያውላቸው ደግሞ በምንም አይረታም፤ መንገዱ የጌታ ብርሃን ነውና።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች