ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 48 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ኤልያስ 1 ነቢዩ ኤልያስ እንደ እሳት ተነሣ፤ ቃሉም እንደ ችቦ ተንቦገቦገ። 2 በእነርሱ ላይ ረሃብን ያመጣ፥ ብዙዎችንም በትጋቱ ያጠፋቸው እርሱ ነው። 3 በጌታ ቃል ሰማያትን ዘጋ፤ ሦስት ጊዜም እሳትን አወረደ። 4 ኤልያስ ሆይ ተአምራቶች ድንቅ ናቸው፤ እንዳንተ ሊመካ የሚችል ይኖራልን? 5 በልዑል እግዚአብሔር ቃል፥ ሙት ከሲኦል ስታስነሣ፥ 6 ነገሠታትን ከሥልጣናቸው፥ ባለሥልጣኖችን ከግዛቶቻቸው፥ ያወረድህ አንተ ነህ። 7 ተግሣጽን በሲና፥ የቅጣት አዋጅን በሆሬብ የሰማህ፥ 8 ተበቃይ ነሥታትን፥ አንተን የሚተኩ ነቢያትንም የቀባህ፥ 9 በእሳት ዓውሎ ነፋስ፥ በእሳታዊ ፈረሶች በማሳብ ሠረገላ የተወሰድህ፥ 10 መቅሠፈቶችን ለመተንበይ፥ መዓቱ ከመውረድ በፊት፥ የእግዚአብሔርን ቁጣ ለማብረድ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው ለመመለስ፥ የያዕቆብን ነገዶች ደግሞ ለማቋቋም፥ የተመረጥህ ነህ። 11 አንተን የሚያዩ፥ በፍቅር ያቀላፉ፥ የተባረኩ ናቸው፤ እኛም በእርግጥ ሕይወት ይኖረናልና። ኤልሳዕ 12 ኤልያስ በአውሎ ነፋስ በተከበበ ጊዜ፥ መንፈሱ በኤልሳዕ አደረ፤ በሕይወት ዘመኑ አንድም ገዥ ሊያስደነግጠው፤ አንገቱንም ሊያስደፋው አልቻለም። 13 ለእርሱ የሚከብድ ነገር አልነበረም፤ ከሞተም በኋላ ትንቢት ተናግሯል። 14 በሕይወት ሳለ ተአምራትን ሠርቷል፤ በሙታን ዓለምም የሚያስገርሙ ተግባራትን ፈጽሟል። ቃል ኪዳንን ማፈረስ እና ቅጣት 15 ይህ ሁሉ ቢደረግም ሕዝቡ አልተጸጸተም፥ ኃጢአት ከመሥራትም አልታቀበም፤ ከሀገራቸው እስኪባረሩና በምድር ሁሉ እስከተበተኑ ድረስ፥ ራሳቸውን አላስተካከሉም። 16 ከዳዊት ቤት የተገኘ አንድ ሹምና፥ ጥቂት ሰዎች ብቻ ቀሩ፤ አንዳንዶቹ ግን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠሩ፤ ሌሎች ደግሞ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ ከመሩ። 17 ሕዝቅያስ ከተማውን በምሽግ አጠናከረ፥ የውኃ ማከፋፈያም አዘጋጀ፥ ቋጥኙን በብረት ፈልፍሎ ዋሻ ሠራ፤ በዚህያም የማጠራቀሚያ ገንዳዎች ገነባ። 18 በእርሱ ዘመን ሴናክሬብ ወረረው፥ ራባስቴስን ላከ፥ እጁን በጽዮን ላይ አነሣ፤ በትዕቢት ተወጥሮም ደነፋ። 19 ያንጊዜ ልቦቻቸውና እጆቻቸው ተንቀጠቀጡ፥ ምጥ እንደጠናባት ሴት ተጨነቁ። 20 ነገር ግን መሐሪውን አምላክ ተማፀኑ፥ እጆቻቸውን ወደ እርሱ ዘረጉ፥ ቅዱስ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ሰማቸው፥ በኢሳይያስም እጅ አዳናቸው፤ 21 እርሱ የአሞራውያንን ሠፈር አፈራረሰ፤ መልአኩም ፈጃቸው። ኢሳይያስ 22 ራእዩ ጠብ በማይለው በታላቁ ነቢይ በኢሳይያስ በታዘዘው መሠረት፥ ሕዝቅያስ ጌታን የሚያስደስት ሥራ ሠራ፤ የአባቱን የዳዊት ፈለግም ተከትሎ ቆራጥነቱን አሳየ። 23 በእርሱ ዘመን ፀሐይ ወደ ኋላ አፈገፈገች፥ የንጉሡንም ዕድሜ አራዘመ። 24 በመንፈስ ኃይል የመጨረሻዎቹን ነገሮች ማየት ቻለ፥ የጽዮንን ኀዘንተኞች አጽናና። 25 እስከ መጨረሻው ዘመን የሚሆነውን፥ የተደበቁትንም ነገሮች ከመሆናቸው አስቀድሞ ገለጸ። |