Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 41 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሞት

1 ሞት ሆይ! ንብረቱን እንደ ያዘ በሰላም ለሚኖር፥ ያለአንዳች ጭንቀት ኑሮውን ለሚመራና በምግብም ለሚደሰት ሰው አንተን ማሰብ ምንኛ ያሰቅቃል!

2 ሞት ሆይ! ኃይሉ ለደከመበትና ችግር ላጐሳቆለው፥ እርጅና ለተጫነውና የሺህ ጭንቀቶች ጐሬ ለሆነው፥ ለቁጡውና ትዕግሥት ላጣው ፍርድህ አስደሳች ነው።

3 የሞትን ፍርድ አትፍሩ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን፥ ከኋላችሁም የሚመጡትን አስቡ።

4 ለፍጡራን ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ይህ ነው፤ መልካም የሆነውን እርሱ ያውቃልና። ስለምን የእርሱን ፈቃድ እንቃወማለን? ለዓሥር፥ ለመቶ ወይም ለሺህ ዓመታት በሕይወት ብትኖር ዕድሜህን በሲኦል ውስጥ አትጠየቅበትም።

5 የኃጢአተኞች ልጆችን የመሰሉ ያልተባረኩ ዘሮች፥ በክፉዎች መናፍስት ጥላ ሥር ይሰበሰባሉ።

6 የክፉዎች ልጆች ውርስ ዕጣው ጥፋት ነው፤ ዘራቸውም ውርደትን ተከናንቦ ይኖራል።

7 ክፉ አባት በልጆቹ ላይ ላመጣው ውርደት፥ በእነርሱው አንደበት ይወቀሳል።

8 የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ የጣሳችሁ፥ እናንት ኃጢአተኞች፥ የተከተላችሁት መንገድ አያዘልቃችሁም።

9 የተወለዳችሁት ለእርግማን፥ በሞታችሁም ጊዜ ድርሻችሁ እርግማን ነው።

10 ከመሬት የተገኘ ሁሉ፥ ወደ እርሷ ይመለሳል፤ ክፉዎችም እንዲሁ ከእርግማን ወደ ጥፋት ያመራሉ።

11 የሚታዘነው ለሙታን በድን ብቻ ነው፤ ዋጋ ቢስ የኃጥአን ስም ግን ይጠፋል።

12 ስለ ክብርህ ተጠንቀቅ፤ ከሺህ የወርቅ ክምር የበለጠ ይኖርሃልና።

13 ጥሩ ሕይወት እድሜው አጭር ነው። መልካም ስም ግን ለዘለዓለም ይኖራል።


ኃፍረት

14 ልጆቼ ሆይ! ትእዛዞቼን ጠብቁ፥ በሰላምም ኑሩ፥ የተደበቀ ጥበብና የማይሰሩበት ሃብት፥ ከቶ ምን ይጠቅማል?

15 ጥበብን ከሚደብቅ ሰው ይልቅ፥ ሞኝነቱን የሚደብቅ ይሻላል።

16 በሁሉም ነገር ማፈር አይገባም፤ ሁሉም ነገር ከሁሉም ሰው ትክክለኛ ግምትን አያገኝም፤ በሚከተሉት ሁኔታዎች ግን ኃፍረት ይሰማህ።

17 በእናትህና በአባትህ ፊት ያልተገባ ፀባይ ስታሳይ፥ በመሪዎችና በልዑላን ፊት ውሸት ስትናገር፥

18 በዳኛው ወይም በሕግ ባለ ሥልጣን ፊት ስትበድል፥ በሕዝብ ጉባኤ ፊት ስታጠፋ፥

19 በጓደኞችህና በወዳጆችህ ፊት ስትወሰልት፥ በጐረቤቶችህም ፊት ስትሰርቅ፥ እፍረት ይሰማህ።

20 በእውነትና በእግዚአብሐር ቃል ኪዳን ፊት፥ በመሠዊያው ላይ በመደገፍህ፥

21 ስትሰጥም ሆነ ስትቀበል ትሕትና ባለማሳየትህ፥ ሰላምታ ላቀረቡልህ ሰላምታ በመንፈግህ፥

22 ጋለሞታዋን ትኩር ብለህ በማየትህ፥ ወገንህን በመግፋትህ፥

23 የሌላውን ድርሻ ወይም ስጦታ የግልህ በማድረግህ፥ የሌላውን ሰው ሚስት በማሽኮርመምህ፥

24 ሴት አገልጋዩን በመመኘትህ፥ ወደ አልጋዋ አትጠጋ

25 ወደጆችህን በማስቀየምህ ከስጦታ በኋላ አትሳለቅ፤

26 የሰማውን ሁሉ በመናገርህ፥ ምሥጢሮችን በማውጣትህ፥ እፍረት ይሰማህ።

27 የኔ እውነተኛ ኀፍረት ምን እንደሆነ ታውቃለህ፤ በሁሉም ሰው ዘንድም ትከበራለህ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች