ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ልጄ ሆይ ለድኃ ለኑሮው የሚያስፈልገውን ስጠው፤ የችግረኞች ዐይኖች በምኞት እንዲቅበዘበዙ አታድርግ። 2 የረሃብተኛውን ሰቆቃ አታባብስ፤ በችግር ላይ የሚገኘውን ሰው አታጥምደው። 3 ለተቆጣ ልብ ጭንቅ አትጨምርበት፤ ለተቸገረ እርዳታህን አታዘግይበት። 4 በጭንቅ ያለ ሰው ሲለምንህ እምቢ አትበለው፤ ፊትህን ከድሆች አትመልስባቸው። 5 ችግረኛን አልመለከትም አትበል፤ ማንንም ቢሆን እንዲረግምህ ዕድል አትስጠው። 6 ኑሮ የመረረው ሰው ቢረግምህ፤ ፈጣሪው እርግማኑን ይሰማል። 7 በማኀበር የተወደድህ ሁን፤ በትልቅ ሰው ፊት ራስህን ዝቅ አድርግ። 8 ጆሮህን ወደ ድሃ ጣል አድርገህ አዳምጥ፤ ሰላምታውንም በትሕትና መልስ፤ 9 ተጨቋኞችን ከጨቋኞች እጅ አድን፤ ፍርድ ስትሰጥ ደካማ አትሁን፤ 10 አባት ለሌላቸው እንደ አባት፥ ለእናቶቻቸውም ደግሞ እንደ መልካም ባል ሁን። ታዲያ አንተም ለልዑል እግዚአብሔር እንደ ልጅ ትሆናለህ፤ ፍቅሩም ከእናትህ ፍቅር የበለጠ ነው። የጥበብ መምህርነት 11 ጥበብ ልጆችዋን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ የሚፈልጓትን ትጠነቀቅላቸዋለች። 12 እርሷን መውደድ ሕይወትን መውደድ ማለት ነው፤ በማለዳ የሚፈልጓትም በደስታ ይሞላሉ። 13 እርሷን ያገኘ ክብርን ይወርሳል፤ በሚሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር ይባርከዋል። 14 እርሷን የሚያገለግሉ ቅድሱን አምላክ ያገለግላሉ፤ እርሷን የሚወዷትን እግዚአብሔር ይወዳቸዋል። 15 እርሷን የሚታዘዝ ሕዝቦችን ይገዛል፥ እርሷን የሚከተል በሰላም ይኖራል። 16 ለእርሷ የታመነ ይወርሳታል፤ የወገኖቹም ንብረት ትሆናለች። 17 በመጀመሪያ በጠመዝማዛ መንገዶች ትወስደዋለች፤ ፍርሃትንና ድንጋጤን ታመጣበታለች፤ እስክታምነው ድረስ በሥርዓቷ ታጠናዋለች፤ በመከራም ትፈትነዋለች። 18 በኋላ በቀጥታ ወደ እርሱ መጥታ ታስደስተዋለች፤ ምሥጢሮችዋም ትገልጥለታለች። 19 ነገር ግን ከሷ ቢርቅ ትተወዋለች፤ ወደ ጥፋትም ትጥለዋለች። ራስን ዝቅ ማድረግና ሌሎችን ማክበር 20 ሁኔታዎችን አይተህ ከክፉ ነገር ተጠበቅ፤ በራስህ አትፈር። 21 ወደ ኃጢአት የሚመራ እፍረት አለ፤ የሚያስከብር ሞገስም ያለው እፍረት አለ። 22 በራስህ ላይ እምብዛም አትጨክን፤ እፍረት ወደ ውድቀት እንዲመራህ አትፍቀድ። 23 መልካም ውጤት ያስገኛል ብለህ ካመንክ ከመናገር ወደኋላ አትበል ጥበብህንም አትደብቅ፤ 24 ጥበብህ የሚታወቀው በአነጋገርህ ነውና፥ አዋቂነትህም በቃላትህ ይመሰከራል። 25 እውነትን ከምትቃረን፤ በድንቁርናህ ብታፍር ይቀላል። 26 ኃጢአትህን ለመናዘዝ አትፈር፤ የጅረትህን ውሃ ለማቆም አትድከም። 27 በሞኝ ፊት ራስህን ዝቅ አታድርግ፤ ለኃይለኞች አትወግን፤ 28 ስለ እውነት እስከ ሞት ታገል፤ እግዚአብሔር አምላክህ ከጐንህ ይዋጋል። 29 በምላስህ ደፋር፥ ይልቁንም በሥራህም ሰነፈና ቸልተኛ አትሁን። 30 በቤትህ አንበሳ፥ አገልጋዮችህን በተመለከተ ፊሪ አትሁን፤ 31 ለመቀበል የሚዘረጉት እጆችህ፥ ለመስጠት አይሰብሰቡ። |