Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 37 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሐሰተኛ ወዳጆች

1 ጓደኛ ሁሉ እኔም እኮ ወዳጅህ ነኝ ይላል፤ አንዳንዶች ግን የስም ወዳጆች ናቸው።

2 ጓድህ ወይም ወዳጅህ ጠላትህ ሲሆን፥ ከልብ አያሳዝንም?

3 ክፋት ሆይ! ምድርን በውስልትና ለማጥለቅለቅ ስለምን ተፈጠርህ?

4 አንደኛው ዓይነት ወዳጅ በተድላ ጊዜ አብሮ ይደሰታል፥ በመከራ ወቅት ግን ይሸሻል።

5 ሌላው ደግሞ ለወዳጁ ተቆርቋሪ ነው፤ በፍልሚያ ወቅት አብሮ መሣሪያ ያነሣል።

6 እውነተኛውን ወዳጅ አትዘንጋ፤ ሀብት ባፈራህም ጊዜ አትርሳው።


አማካሪዎች

7 አማካሪ ሁሉ ምክርን ይለግሳል፥ አንዳንዶች ግን ለፍላጐታቸው የተገዙ ናቸው።

8 ምክርን ከሚሰጥ ሰው ተጠበቅ፤ እርሱ የሚሻውንም ቀድመህ እወቅ። ምክሩ የፍላጐቱ ውጤት በመሆኑ ባንተ ላይ ሊያሴር ይችላልና።

9 ትክክለኛውን ፈር ተከትለሃል ይልሃል፤ ካንተ ርቆ ግን ምን እንደሚያደርስብህ ይመለክታል።

10 የጐሪጥ ከሚያይህ ሰው ምክርን አትጠይቅ፤ ባንተ ከሚቀኑ ሰዎች ሐሳብህን ደብቅ።

11 ሴትን ስለጣውንቷ፥ ፊሪን ስለ ጦርነት፥ ነጋዴን ስለዋጋ፥ ሸማችን ስለገበያ፥ ባለጌን ስለ ውለታ፥ ራስ ወዳዱን ስለ ደግነት፥ ሰነፉን ስለ ሥራ፥ ዳተኛውን ስለ ሥራው ፍጻሜ፥ ሀኬተኛውን አገልገይ ስለ አስቸጋሪው ሥራ አትጠይቃቸው። ከእነርሱ የሚመጣውንም ምክር አትቀበል።

12 ትእዛዛትን ከሚፈጽመው ጻድቅ ሰው፥ ነፍሱ ነፍስህን ከምትመስለው ሰው፥ ብትበድል እንኳ ከሚያዝንልህ ሰው ዘንድ አትራቅ።

13 ልብህ ከምትለግስህ ምክር አትውጣ፤ ከእርሷ የበለጠ ታማኝ የሚሆንህ የለምና፤

14 ማማ ላይ ከሚቆሙ ሰባት ቃፊሮች ይልቅ፥ ነፍስህ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ትሰጥሃለችና።

15 ከነኚህም ሌላ ወደ እውነት ይመራህ ዘንድ፥ ልዑል እግዚአብሔርን ለምን።


ትክክለኛና ሐሰተኛ ጥበብ

16 ለማንኛውም ተግባር መሠረቱ፥ መርምር መሆን አለበት። ከማንኛውም እንቅስቃሴ በፊት፥ ማሰብ መቅደም ይኖርበታል።

17 የሐሳቦች ሥረ መሠረት ልብ ነው፤ አራት ቅርንጫፎችን ያበቅላል።

18 እነርሱም፥ ደግና ክፉ፥ ሕይወትና ሞት ናቸው። የሁሉም እመቤት ደግሞ ምላስ ናት።

19 አንዳንዱ ሌሎቹን ለማስተማር ብቁ ነው፤ ለራሱ ግን አያውቅም።

20 ንግግር አዋቂው ደግሞ የተጠላ ነው፤ መጨረሻውም በጠኔ መሞት ነው፤

21 ጥበብ የተነፈገው፥ የእግዚአብሔርንም ቸርነት ያላገኘ ነውና።

22 ሌላው ራሱን አዋቂ ያደርጋል፤ በጥበቡ የሚደርስበትንም ድምዳሜ ሐቅ ነው ይላል።

23 እውነተኛው ጠቢብ ግን ሕዝቡን ያስተምራል፤ የጥበብም ፍሬ ይጐመራል፤

24 ጥበበኛ ሰው ምርቃት ይጐርፍለታል፤ ያዩት ሁሉ ደስተኛ ነህ ይሉታል።

25 የሰው ሕይወት ቀናቱ የተወሰኑ ናቸው፤ የእስራኤል ግን አይቆጠርም።

26 ጥበበኛ ሰው በሕዝቡ ዘንድ የታመነ ነው፤ ስሙም ለዘለዓለም ሕያው ይሆናል።


መመጠን

27 ልጄ ሆይ! በሕይወት ዘመንህ ለጤናህ የሚስማማህን ፈልግ፤ ለእርሱ የማይስማማውን አታቅርብለት፤

28 ሁሉም ነገር ለሁሉም ሰው ተስማሚ ሊሆኑ፥ ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር ሊወድ አይችልምና።

29 ውበትን ሁሉ አልጠግብ ባይ አትሁን። ለምግብ አትሰስት።

30 ከመጠን በላይ መብላት ሕመምን፥ ገደብ የለሽም መሆን የጉበት መነካትን ያስከትላል።

31 በቁንጣን ሳቢያ ብዙዎች አልቀዋል፤ ዕድሜህን ለማርዘም ራስህን ተቆጣጠር።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች