Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 35 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሕጉና መሥዋዕቶች

1 ሕጉን የሚፈጽም ብዙ መባ እንዳቀረበ ይቆጠርለታል። ትእዛዛቱን የሚያከብር የኀብረት መሥዋዕቶችን ያቀርባል።

2 የውለታ መላሽነት ማረጋገጫ የዱቄት መባ ነው፤ መመጽወት የምስጋና መሥዋዕት ነው።

3 ከክፋት መራቅ እግዚአብሔርን ያስደስታል፤ ከበደል መታቀብ የማስተሥረያ መሥዋዕት ነው።

4 በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጅህን አትቅረብ፤ እነኚህ ሁሉ ትእዛዛቱ ናቸውና።

5 የእውነተኞች መባ መሠውያውን ግርማ ያጐናጽፈዋል፤ መዓዛውም ከልዑል እግዚአብሔር ፊት ይቀርባል።

6 የጻድቃን መሥዋዕት ተቀባይነት አለው፥ መታሰቢያውም አይዘነጋም።

7 በቸርነትህ እግዚአብሔርን አክብር፤ በኵራትህም ስታቀርብ አትሰስት።

8 ስጦታዎችህን ስታቀርብ ከፈገግታ ጋር ይሁን፤ እሥራትህን በደስታ አቅርብ።

9 እግዚአብሔር እንደሰጠህ ሁሉ ለእርሱም ሰጠ፤ ይህንንም አቅምህ እንደሚፈቅድ አድርግ።

10 እግዚአብሔር ለጋስ ስለሆነ ሰባት ጊዜ እጥፍ ይሰጥሃል።


መለኮታዊ ፍትሕ

11 ስጦታዎችን በመማለጃነት አታቅርብ፥ እርሱ አይቀበልህምና። በቅንነት ባልቀረቡ መሥዋዕቶች ላይ እምነት አትጣል፤

12 እግዚአብሔር አድልዎን የሚያውቅ ፍጹም ዳኛ ነውና።

13 ስለድሆች መጐዳት አያዳላም፤ የተጐዳውን ወገን አቤቱታም ያዳምጣል።

14 የሙት ልጅ የሚያቀርቡለትን ልመና አይዘነጋም፤ የመበለቷንም መሬት ቸል አይልም።

15 ለመከራው ምክንያት የሆነውን ሰው ስትከስ፥ የመበለትዋ እንባ በጉንጮችዋ አይወርድምን?

16 በሙሉ ልብ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነ ሰው ተቀባይነትን ያገኛል፤ ልመናውም እስከ ሰማይ ይደርሳል።

17 የትሑት ሰው ጸሎት ደመናትን ያቋርጣል። ከፈጣሪም ዘንድ እስኪደርስ አይጽናናም።

18 ልዑል እግዚአብሔር ወደ እርሱ እስካላየ ድረስ፤ ጻድቃንም ፍትሕን ካላገኙ በቀር ጸሎቱን አያቋርጥም።

19 እግዚአብሔርም፥

20 ጨካኞችን ካላኮላሸ፥ በመንግስታቱ ላይ ካልተበቀለ፥

21 የግትሮችን ክምር ካልናደ፥ የበደለኞችን በትረ መንግሥት ካልሰበረ፥

22 ለሰው ሁሉ እንደ ሥራው ካልከፈለ፥ ድርጊቶቻቸውም እንደ አነሳሳቸው ዋጋ ካላገኙ፥

23 የሕዝቡን ሁናቴ መርምሮ በምሕረቱ ካላስደሰታቸው አይታገሥም። ስለ እነርሱም ሲል አይዘገይም።

24 በመከራ ጊዜ የሚገኝ ምሕረት፥ በድርቅ ወቅት እንደሚታዩ የዝናብ ደመናዎች ያስደስታል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች