Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 34 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ከንቱና የማይጨበጥ ተስፋ የሞኞች ነው፤ ሕልሞችም ለእንርሱ ክንፍ ይሰጧቸዋል።

2 ሕልሞችን ማመን ጥላን እንደ መጨበጥና ነፋስን እንደማባረር ነው።

3 ሕልሞች ከመስተዋቶች አይለዩም፤ የፊትህ ነጸብራቅ መልሶ ያይሃል።

4 ባለመንጻት የሚነጻ፥ በሐሰትስ የሚረጋገጥ ምንድነው?

5 ጥንቆላ፥ ገድና ሕልም፥ እንደ ነፍስ ጡር ቅዠት አይጨበጡም።

6 ከልዑል እግዚአብሔር ካልተላኩ በቀር አትጨነቁላቸው።

7 እነርሱን ያመኑ ብዙዎች ጠፍተዋል፤ ተስፋቸውንም በእነርሱ ላይ ያደረጉ ሰዎች ኀዘን ላይ ወድቀዋል።

8 ሕጉን መፈጸም ግን ይህን የመሰለ ሐሰት አይሻም፤ ጥበብም ስለ ትክክለኛነቷ ፍጹም ናት።

9 ብዙ ቦታዎችን ያዩ ብዙ ያውቃሉ፤ ልምድ ያለው ሰው የሚናገረውም ከመሬት አይወድቅም።

10 ያልተፈተነ ሰው ዕውቀቱ ጥቂት ነው፤ ተጓዥ ሰው ግን ሁሉንም ያውቃል።

11 በጉዞዎቼ ላይ ብዙ ነገር አየሁ፤ በቃላት ከምገልጸውም በላይ ተገነዘብሁ።

12 ብዙ ጊዜ የሞት ጥላ አንዣቦብኛል፤ ይሁን እንጂ ተርፌያለሁ። ምክንያቱም እንዲህ ነው፥

13 እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች መንፈስ ሕያው ነች።

14 እግዚአብሔርን የሚፈራ ከቶውንም ሊጠራጠር አይገባም፤ ተስፋውም በጌታ ነውና አይፈራም።

15 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነፍስ ትደሰት፤ የሚተማመነው በማነው? ረዳቱስ ማነው?

16 እርሱን የሚወድትን ሁሉ የአምላክ ዐይኖች ይከታተላሉ። የማይደፈረው ጠባቂያቸው፥ ጠንካራውም ደጋፊያቸው እርሱ ነው። የበረሃው ነፋስ ከለላ፥ የቀን ሐሩር ጥላ፥ ከመከራ ጠባቂ፥ ከውድቀታቸውም አዳኛቸው ነው።

17 እርሱ መንፈስን ያድሳል፤ ዐይኖችን ያበራል፤ ጤና፥ ሕይወትንና በረከትን ይሰጣል።


መሥዋዕቶች

18 ፍትሕን በማጓደል የተገኘውን ስጦታ፥ በመሥዋዕትነት ማቅረብ ማላገጥ ነው። የክፉ ሰው ስጦታዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም።

19 ልዑል እግዚአብሔር ከበደለኞች በሚቀርቡ ስጦታዎች ደስ አይሰኝም፤ የመሥዋዕቶች ብዛት ኃጢአትን ይቅር አያሰኝም።

20 ከድሆች ሀብት ተነጥቆ የሚቀርብ መሥዋዕት፥ ልጁን በአባቱ ፊት እንደ መሠዋት የከፋ ነው።

21 ቁራሽ እንጀራ የችግረኞች ሕይወት ነው፤ ከአፋቸው ላይ እርሷኑ መንጠቅ ነፍስ ማጥፋት ነው።

22 የሰውን መተዳደሪያ መንጠቅ ያው መግደል ነው፤

23 አንዱ ቢያፈርስ፥ ሌላው ቢገነባ፥ ከድካም በቀር ምን ያተርፋሉ?

24 አንደኛው ሲጸልይ ሌላኛው ቢራገም፥ ጌታ የሚያደምጠው የትኛውን ነው?

25 አንዱ ሬሳ ነክቶ እጁን ቢታጠብ፥ ዳግመኛም ቢነካው የመታጠቡ ትርጒም ከምኑ ላይ ነው?

26 ለኃጢአት ስርየት የሚጾም ሰው፥ ዳግም የሚበድል ከሆነም እንዲሁ ነው። የዚያን ሰው ጸሎት ማን ይሰማዋል? ራስን ማዋረድ ምን ይጠቅማል?

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች