ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 33 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 እግዚአብሐርን የሚፈራ ክፉ ነገር አያገኘውም፤ በመከራ ጊዜ እንኳ ይድናል። 2 ሕጉን የሚጠላ ጠቢብ አይደለም፤ ግብዝም ሰው በማዕበል እንደሚንገላታ መርከብ ነው። 3 አዋቂ ሰው በሕጉ ያምናል፤ እንደ ትንቢትም ይቀበለዋል፤ 4 የምትናገረውን አዘጋጅ፤ አድማጭ ታገኛለህ፤ መልስም ከመስጠትህ በፊት መረጃዎችህን አጠናቅር። 5 የሞኝ ስሜት እንደ ጋሪ እግር ነው፤ አስተሳሰቡም እንደ ቅትር ይሽከረከራል። 6 ድንጉላ ፈረስ እንደ አሽሟጣጭ ወዳጅ ነው፤ ማንም ቢጋለበው ያሸካካል። ልዩነት 7 ፀሐይ በዓመቱ ባሉት ቀናት እኩል ብርሃን ብትለግስም፥ ስለምን አንድ ቀን ከሌላው የተሻለ ይሆናል? 8 በዓላትንና ወቅቶችን ይለያየው ጌታ፥ እነርሱንም ለያይቷቸዋል። 9 ከፊሎቹን ታላቅና የተቀደሱ፤ ሌሎቹን ደግሞ ተራ አድርጓቸዋል። 10 የሰው ልጆች የተገኙት ከምድር ነው። አዳምም የተፈጠረው ከአፈር ነው። 11 እግዚአብሔር በታላቅ ጥበቡ የተለያዩ አድርጓቸዋል፤ አኗኗራቸውም ለየግል ነው። 12 አንዳንዶቹን ባርኳቸዋል፥ ቀድሷቸዋል፤ ወደ እርሱም አቅርቧቸዋል። ሌሎቹን ደግሞ ረግሟቸዋል፥ አዋርዷቸዋል፤ ከሥልናቸው ነቅሎ ጥሏቸዋል። 13 ሸክላ ሠሪው ጭቃውን በፈለገው መልክ እንደሚቀርጸው ሁሉ፥ በፈጣሪያቸው እጅ ያሉት ሰዎችም እንዲሁ በፍርዱ መሠረት የሚገባቸውን ያገኛሉ። 14 በክፋት ፊት ደግነት፥ በሞት ፊት ሕይወት እንዳለ ሁሉ፥ በጻድቁም ፊት ኃጢአተኛው ይቆማል። 15 የልዑል እግዚአብሔርን ሥራዎች ብትመረምር፥ ሁሉም ጥንድና ተቃራኒ ሆነው ታገኛቸዋለህ። 16 ከሁሉም መጨረሻ የመጣሁ እኔ ብሆን፥ ከወይን ቆራጮች የተረፈውነ እንደሚሰበስበው ሰው ዓይኔ ሁሉንም ይመለከት ነበር። 17 በእግዚአብሔር ቡራኬ ቀድሜ ገባሁ፤ እንደ ትክክለኛው የወይን ቆራጭ፥ መጭመቂያዬንም ሞላሁ። 18 የምሠራውም ለግሌ እንዳልነበር አስተውል፤ ትምህርት ለሚሹ ሁሉ እንጂ። 19 የተከበራችሁ የሕዝብ መሪዎች አድመጡኝ! የጉባኤው ሰብሳቢዎችም ጆሯችሁን አውሱኝ። ነጻነት 20 በሕይወት ዘመንህ፥ ለልጅህም ሆነ ለሚስትህ፥ ለወንድምህም ሆነ ለወዳጅህ፥ ባንተ ላይ ሥልጣንን አትስጣቸው። ሐብትህንም ቢሆን ለማንም አትስጥ፤ ድንገት እንኳ ብትቆጭ፥ መልሱልኝ ብለህ መጠየቅ ይኖርብሃልና። 21 በሕይወት እስካለህና እስትንፋስህ እስካልቆመች ድረስ፥ ባንተ ያዝ ዘንድ ለማንም ሥልጣንን አትስጥ። 22 አንተ የእነርሱን ፊት ከምታይ፥ ልጆችህ አንተን ቢለምኑህ ይሻላል። 23 በምትሠራው ሁሉ ኃላፊው አንተ ሁን፤ ክብርህንም ሳታዋርድ እለፍ። 24 ሞት በላይህ ባንዣበበ ጊዜ፥ በመጨረሻዋ ሰዓት ውርስህን አከፋፍል። አገልጋዮች 25 ድርቆሽ፥ ዱላና ሸክም ለአህያ፥ እንጀራ፥ ሥርዓትና ሥራ ደግሞ ለአገልጋይ ነው። 26 አገልጋይህን ከጠመድከው የአእምሮ ሰላምን ታገኛለህ፤ ሥራ ፈትቶ ከተቀመጠ ግን ነጻነቴን ይልሃል። 27 ቀንበርና ልጓም አንገት ያስደፋሉ፤ ቅጣትና ሥቃዩም እንዲሁ መጥፎ አገልጋይን ያርማሉ። 28 ሥራ ፈትቶ እንዳይቀመጥ አሠራው፤ ሥራ ፈትነት ተንኮልን ያስተምራል። 29 ከሥራው ፈቀቅ እንዳይል አድርግ፤ አልታዘዝም ካለ እሠረው። 30 ግና ማንንም ቢሆን ከሚገባው በላይ አትቅጣ፤ ፍትሕን አታዛባ። 31 አገልጋይህ አንድ ብቻ ነውን? በደም ያገኘኸው ነውና እንደ ራስህ እየው። አገልጋይህ አንድ ብቻ ነውን? ራስህን እንደምትፈልገው ሁሉ፤ እርሱም ያስፈልግሃልና እንደ ወንድምህ እየው። 32 በአግባቡ ባትይዘው ግን ትቶህ ይኮበልላል፤ 33 በየትኛውስ መንገድ ልትፈልገው ትሄዳለህ? |