ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 30 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የልጆች አስተዳደግ 1 ልጁን የሚወድ ሁሉ አዘውትሮ ይቀጣዋል፤ ለወደፊትም በልጁ ይደሰታል። 2 ልጁን የሚቆጣጠር የድካሙን ፍሬ ይሰበስባል፤ በሚያውቁት ሰዎችም ፊት በልጁ ይኮራል። 3 ልጁን የሚያስተምር ጠላቱ ይቀናበታል፤ በወዳጆቹም መካከል በልጁ ይኮራል። 4 አባቱ ቢሞት ሕያው ነው፤ መሳዩን ትቶ አልፏልና። 5 በሕይወቱ ከልጁ ጋር ደስታን ተቋድሷል። ሞት በመጣ ጊዜም ስጋት የለበትም። 6 ጠላቶቹን የሚበቀልበት፤ ወሮታውን የሚከፍልለት ልጅ ተክቷል። 7 ልጅን የሚያንቀባርር ቁስሉን ይሸፈናል፤ ባለቀሰም ቍጥር አንጀቱ ይላወሳል። 8 በደንብ ያልተገራ ፈረስ ያገረግራል፤ አግድም አደግ ልጅም አይታዘዝም። 9 ልጅህን አሞላቅ፥ ያስደነግጥሃል። ከእርሱ ጋር ተጫወት፥ ያሳዝንሃል። 10 አትሳቅበት፥ ያስለቅስሃል፥ ጥርስህንም ያስነክስሃል። 11 በወጣትነቱ ነጻነት አትስጠው፤ ሲያጠፋም አትለፈው። 12 በወጣትነቱ እንዲታዘዝህ ቅጣው፤ በልጅነቱ ጐን ጐኑን ሸንቁጠው። ካልተቀጣ ግን ግትርና ስድ ሆኖ ያድጋል፤ በጣምም ያሳዝንሃል። 13 ልጅህን ተከታተል፥ ለአፍታም ቸል አትበለው፤ ካልሆነ ግን በአጥፊነቱ ትጸጸታለህ። ጤና 14 ጤነኛና ብርቱ ሆኖ መደኸየት፥ ሃብታም ሆኖ ከመሰቃየት ይሻላል። 15 ከወርቅ ይልቅ ጤናና ብርታት፥ ከብዙ ሃብታም ጠንካራ አካል ይመረጣል። 16 ከጤና የሚበልጥ ሃብት፥ ከመንፈስ ደስታም የሚበልጥ እርካታ የለም። 17 ከመከራ ሕይወት ሞት፥ ከማይለቅ ደዌም ዘለለማዊ ዕረፍት ይሻላል። 18 ለተዘጋ አፍ የሚቀርብ ጣፋጭ ምግብ፥ በመቃብር ላይ እንደሚቀርብ የምግብ መባ ነው። 19 መብላትም ሆነ መጠጣት ለማይችል ጣዖት መሥዋዕት ማቅረብ ከቶ ምን ይጠቅማል? እግዚአብሔርም በደዌ የቀሰፈው ሰው እንዲሁ ነው። 20 ቆንጆ ጉብል አቅፎ እንደሚያቃስ ጃንደረባ፥ እርሱም ያያል፥ ሲቃም ይይዘዋል። ደስታ 21 ራስህን አታሳዝን፤ በሐሳብም አትጨነቅ። 22 የልብ ደስታ ሕይወት ነው፤ የዕድሜም ምንጩ እርሱ ነው። 23 ነፍስህን አስደስት፥ ልብህን አጽናና፥ ኀዘንን ከፊትህ አባርር፥ በእርሱ ምክንያት የብዙዎች ሕይወት ተበላሽቷል፤ ማንንም አይጠቅምምና። 24 ቅናትና ቁጣ ዕድሜን ያሳጥራል፤ ጭንቀትም ያለ ዕድሜ ያስረጃል። 25 ደስተኛ ልብ የምግብ አምሮትን ያዳብራል፤ መልካም አመጋገብንም ያስለምዳል። |