ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ልጆች በወላጆቻቸው ፊት ያለባቸው ግዴታ 1 ልጆች ሆይ! የኔን የአባታችሁን ምክር ስሙ። ለመዳን የምነግራችሁን ፈጽሙ፤ በእርሱም ተጠበቁ። 2 ጌታ አባትን ከልጆቹ በላይ ያከብራል፤ የእናትንም መብት ከልጆችዋ በላይ ይጠብቃል። 3 አባቱን የሚያከብር ኃጢአቶቹን ያስተሰርያል፤ 4 እናቱን የሚያከብር ሃብት እንደሚያሰባስብ ሰው ነው። 5 አባቱን የማያከብር በልጆቹ ደስታን ያገኛል፤ እርዳታን በለመነ ዕለት ጸሎቱ ይሰማል። 6 አባቱን የሚያከብር ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል፤ ለጌታ የሚታዘዝ እናቱን ደስ ያሰኛል፤ 7 ጌቶችን እንደሚያገለግል ወላጆቹን ያገለግላቸዋል፤ 8 የአባትህን ምርቃት ታገኝ ዘንድ፤ በቃልህም፥ በምግባርህም አክብረው። 9 የአባት ምረቃ የልጆቹን ቤት ያጸናል፤ የእናት እርግማን ግን ሥርን ይነቅላል። 10 በአባትህ ውርደት አትኩራ፤ የአባትህ ውርደት ላንተ ክብር አይደለም። 11 የሰው ክብሩ የሚመነጨው ለአባቱ ካለው አክብሮት ነው፤ ክብሯን የማትጠብቅ እናትም ለልጆችዋ እፍረት ነች። 12 ልጄ ሆይ በሸምግልና ዘመኑ አባትህን ደግፈው፤ በሕይወቱም ሳለ አታሳዝነው። 13 አእምሮውን ቢስትም ራራለት፤ ጤነኛና ጠንካራ በመሆንህ እርሱን አትናቀው። 14 ለአባትህ የዋልከው ደግነት አይዘነጋም፤ ለኃጢአትህ ይቅርታን ያስገኝለሃል እንጂ፤ 15 በመከራ ጊዜ እግዚአብሔር ያስታውስሃል፤ ፀሐይ እንደመታው ውርጭ ኃጢአቶችህ ይቀልጣሉ። 16 አባቱን የሚክድ አምላክን እንዳዋረደ ይቆጠራል። እናቱን የሚያሳዝን በጌታ የተረገመ ነው። 17 ልጄ ሆይ የምትሠራውን ሁሉ፥ በደግነት አድርገው፤ ከፍተኛ ስጦታዎችን ከሚያበረክት ሰው አብልጦ ትወደዳለህ። 18 ታላቅነትህ ባደገ መጠን ትሕትናህም ይጨምር፤ ያንጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ታገኛለህ። 20 የእግዚአብሔር ሥልጣን ከፍ ያለ ቢሆንም፤ የትሑታኑን አክብሮት ይቀበላል። 21 እጅግ የሚከብዱህ ነገሮችን ለማወቅ አትሞክር፤ ከአቅምህ በላይ ስለሆነ ነገር አትመራመር። 22 በተሰጡህ ነገሮች ላይ አተኩር፤ ስለ ምሥጢራት አትጨነቅ፤ 23 ከአቅምህ በላይ የሆኑት ጉዳዮች ውስጥ እጅህን አታስገባ። እስካሁን የተማርኸው ከሰው ልጅ አእምሮ አድማስ ይሰፋል። 24 ብዙዎች በራሳቸው የተሳሳተ አመለካከት ተሰናክለዋል፤ መጥፎ አስተሳሰባቸው የኀሊና ፍርዳቸውን አዛብቶባቸዋል። ትጋት 25 ያለ ዐይን ብሌን ብርሃን አይኖርም፤ ያለ እውቀትም ጥበብ የለም። 26 ሐሳበ ግትር አወዳዳቁ መጥፎ ነው፤ በአደጋ የሚጫወት ራሱን ያጣል። 27 ሐሳበ ግትር መከራ ይበዛበታል፤ ኃጢአተኛ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ይከምራል። 28 የትዕቢተኛው ሕመም ፈውስ አይገኝለትም፤ ምክንያቱም የክፋት ተክል በሱ ውስጥ ሥር ሰዷል። 29 አስተዋይ ልቦና ምሳሌዎችን ያሰላስላል፤ ንቁ ጆሮ የጥበበኛ ምኞት ነው። ምጽዋት 30 ውሃ የሚንበለበለውን እሳት እንደሚያጠፋ፥ እንዲሁም ምጽዋት ኃጢአትን ያነጻል። 31 ለሰዎች የሚለግስ ሁሉ በምትኩ መጪውን ያስባል፤ ለመውደቅ ሲንገዳገድ ደጋፊ ያገኛል። |