ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 29 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ብድር 1 ለባልጀራህ ማበደር የምሕረት ሥራ ነው፤ የዕርዳታ እጅህን መዘርጋት፤ ትእዛዛቱን ማክበር ነው። 2 ባልንጀራህ ሲቸገር አበድረው፤ አንተም ብድርህን በወቅቱ መልስለት። 3 ቃልህን አክብር፤ ለእርሱ ታማኝ ሁን፤ ሁልጊዜም የሚያስፈልግህን ታገኛለህ። 4 ብዙዎች ብድርን ንፋስ እንደጣለው ፍሬ ይቆጥሩታል፤ በችግራቸውም ጊዜ የደረሱላቸውን ሰዎች ያስቀይማሉ። 5 ሰው የሚፈልገውን እስኪያገኝ የባልንጀራውን እጅ ይስማል፤ ስለ አበዳሪውም ሀብት በትሕትና ይናገራል። የመክፈያው ጊዜ ሲደርስ ግን ቀኑን ያስተላልፋል፤ እንዳመጣለት ይናገራል፤ ጊዜውም እንዲራዘምለት ይጠይቃል። 6 እንዲከፍል ቢገደድ እንኳ አበዳሪው ግማሹን ብቻ ቢያገኝ ነው፤ ያንንም እንደ ትልቅ ዕድል ይቆጥረዋል። ካልሆነ ግን ገንዘቡን ተነጥቆ በራሱም ላይ ጠላትን ያፈራል። ወሮታውም፥ እርግማንና ውርደት በክብርም ፈንታ ስድብ ይሆናል። 7 ብዙዎች ለማበደር አይፈቅዱም፤ ከልብ ክፋት የመነጨ አይደለም፤ ገንዘባቸውን ላለማስነጠቅ ሲሉ እንጂ። ምጽዋት 8 ለድሆች ግን ለጋስ ሁን፤ ቸርነትህን ያገኙም ዘንድ አታስጠብቃቸው፤ 9 ትእዛዙን በማክበር ችግረኞችን እርዳ፤ በመከራም ጊዜ ባዶ እጃቸውን አትሸኛቸው። 10 ወንድምህን ወይም ወዳጅህን በገንዘብህ እርዳ፤ ብትቀብረውም ይበሰብሳልና። 11 ልዑል እግዚአብሔር እንዳዘዘው በሀብትህ ተጠቀም፤ ትእዛዙን መፈጸምህ ከወርቅ የተሻለ ትርፍ ይሆንልሃል። 12 ጐተራዎችህን በምጽዋት ሙላ፤ ምግባርህም ከአደጋ ሁሉ ይሰውርሃል። 13 ከጠንካራ ጋሻ፥ ከከባድ ጦርም ይልቅ፥ ከጠላቶችህ ጋር ይዋጋልሃል። ዋስትናዎች 14 ደግ ሰው ባለእንጀራውን ይዋሳል፤ ዕረፍተ ቢስ ሰው ግን ጥሎት ይሄዳል። 15 ዋስህ የዋለልህን ውለታ አትርሳ፤ ላንተ ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል። 16 ኃጢአተኛ ስለ ዋሱ ደኀንነት አያስብም፤ ምስጋና ቢሱ አዳኙን ይረሳል፤ 17 ዋስትና ብዙ ባለጸጐችን አክስሯል፤ በባሕር ማዕበልም ውስጥ ጥሏቸዋል። 18 ኃያላኑን ከቤታቸው አባርሯል፤ በባሕር ማዕበልም ውስጥ ጥሏቸዋል። 19 ለትርፍ ሲል ዋስ ለመሆን የሚፈጥን፥ ፍርድን ለመቀበል ይጣደፋል። 20 ባልንጀራህን እንደ አቅምህ እርዳ፤ እንደ እርሱ ችግር ላይ እንዳትወድቅ ግን ተጠንቀቅ። 21 ለሕይወት የሚያሰፈልጉ ዋነኛ ነገሮች፥ ሙያ፥ እንጀራና ልብስ ናቸው፤ የግል ኑሮን ለመምራት ደግሞ መጠለያ ያስፈልጋል። 22 በሌላ ሰው ቤት ደልቶህ ከመኖር፥ በደሳሳ ጐጆህ ውስጥ ሕይወትህን መምራት ይሻላል። 23 ብዙም ይኑርህ ጥቂት ባለህ ተደሰት፤ ከቤተሰቦችህም ምሬት አትሰማም። 24 ከቤት እቤት መቀየር አስቸጋሪ ሕይወት ነው። የትም ብትሄድ ለመናገር አትደፍርም። 25 የእነርሱ አይደለህም፤ ለምትቀዳው መጠጥ አትመሰገንም፤ ንግግራቸውም ያንገበግብሃል። 26 ና ወዲህ አንተ ባይተዋር ማዕድ አዘጋጅ፤ ምን ይኖርሃል? የሚበላ ነገር ስጠኝ! 27 ባይተዋር ቦታ ፈልግ፤ ታላቅ እንግዳ መጥቶብኛል፤ ወንድሜ ከእኔ ዘንድ ያርፋል፤ ቤቱን እፈልገዋለሁ፤ ትባላለህ። 28 እንደ እንግዳ አለመስተናገድ፥ እንደ ባለዕዳ ውርደትን መቀበል፥ ለአዋቂ ሰው እጅጉን ይከብዳል። |