ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 28 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ተበቃዩን እግዚአብሔር ይበቀለዋል፤ እርሱ ኃጢአትን ይከታተላልና። 2 የጐረቤትህን በደል ይቅር ብትል፥ በጸለይህ ጊዜ ኃጢአትህ ይሠረይልሃል። 3 አንዱ በሌላው ላይ ከተቆጣ፥ እንደምን ከጌታ ርኀራኄን ሊለምን ይችላል? 4 ሰው ለመሰሉ ርኀራኄ ከሌለው፥ ኃጢአቱ ይሠረይለት ዘንድ መለመን ይቻለዋልን? 5 ሥጋ ለባሽ ሆኖ እርሱ ካቄመ፤ ኃጢአቶቹን ማን ያስተሰርይለታል? 6 የመጨረሻዎቹን ቅጣቶች አስታውስ፤ ሞትንና መበስበስን አስብ፤ የእግዚአብሔርንም ትእዛዞች ፈጽም። 7 ትእዛዛቱን አስብ፤ በባልንጀራህ ላይ ክፉ አትመኝ፤ የልዑል እግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አስታውስ፤ የተፈጸመብህንም በደል እለፈው። ፀብ 8 ፀብን አሰወግድ፥ ኃጢአት አታብዛ፤ ቁጡ ሰው ፀብን ያባብሳልና። 9 ኃጢአተኛ ሰው በወዳጆች መካከል ችግርን ይዘራል፤ ሰላም በሰፈነበት አለመግባባትን ይፈጥራል፤ 10 እንደ ማገዶው ብዛት እሳቱ ይነዳል፤ የፀቡም ስፋት ከቁጣው መጠን ጋር ሲተያይ እንዲሁ ነው። የሰው ንዴቱ እንደ ጥንካሬው፥ የቁጣውም መጦፍ እንደ ሃብቱ ነው። 11 ድንገተኛ ፀብ እሳት ይለኩሳል፤ ፈጣን ክርክር ደም ያፋስሳል። 12 ፍምን እፍ ብትላት ትነዳለች፤ ብትተፋባት ትጠፋለች፤ ሁለቱም የአፍህ ውጤቶች ናቸው። ምላስ 13 ተንኮለኛና አሾክሻኪ ሰው የተረገመ ይሁን፤ በሰላም የሚኖሩትን አበጣብጧልና። 14 ሦስተኛዋም ምላስ የብዙዎችን ሰላም አናግታለች፤ ከሀገር ሀገርም እንዲሰደዱ ምክንያት ሆናለች፤ ከተሞችን አውድማለች፥ የታላላቶቹን ቤት አፍርሳለች። 15 ሦስተኛዋ ምላስ ትክክለኛ ሚስቶችን አፋታለች፥ 16 እርሷን የሚሰማ የአእምሮ ዕረፍት አይኖረውም፤ ሰላምም ከእርሱ ትርቃለች። 17 ጅራፍ ሰንበር ያወጣል፤ ምላስ ግን አጥንት ይሰብራል። 18 ብዙዎች ተሠይፈዋል፤ የበለጡ ደግሞ በምላስ ወድቀዋል። 19 ከምላስ ያመለጠ፤ በቁጣዋ ያልተነካ፥ ቀንበሯን ያልተሸከመ፥ በሰንሰለቶቿም ያልተተበተበ የተባረከ ነው፤ 20 ቀንበሯ የብረት፥ ሰንሰለቶቿም ከነሐስ ናቸውና። 21 የምታመጣው ሞት አስከፊ ነው፤ ከእርሱ ሲኦል ይመረጣል። 22 ጻድቃንን ማጥመድ አይቻላትም፤ በነበልባሏም አይነድዱም። 23 ጌታን የሚርቁ ሁሉ ወደ እርሷ ይወድቃሉ፤ በመካከላቸውም ያለማቋረጥ ትነዳለች። እንደ አንበሳ ጉብ ትልባቸዋለች፤ እንደ ነብርም ትቦጫጭቃቸዋለች። 24 ግቢህን በእሾህ አጥር እንድታጥር አትዘንጋ፤ ብርና ወርቅህንም ቆልፈህ አኑር፤ 25 ለቃልህ ሚዛንና ልክ አብጅ፥ ለአፍህም በርና ቁልፍ ይኑርህ። 26 ምላስህ እንዳታደናቅፍህ ተጠንቀቅ፤ ከወደቅህ አድፍጦ ለሚጠብቅህ ግዳይ ትሆናለህና። |