Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 27 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ለትርፍ ሲሉ ብዙዎች በኃጢአት ወድቀዋል፥ ሃብታም ለመሆን የሚሻ እያየ እንዳላየ ይሆናል።

2 ችካል በሁለት ድንጋዮች መካከል ሳይዛነፍ እንደሚቆም ሁሉ፥ በመሸጥና በመግዛትም መሀል እንዲሁ ኃጢአት ይገባል።

3 እግዚአብሔርን በመፍራት ጸንቶ የሚይኖር ሁሉ፥ ሳይዘገይ ቤቱ ይፈርሳል።


ንግግር

4 አሠር በወንፊት ላይ እንደሚቀር፥ የሰው ጉድለቱም እንዲሁ በንግግሩ ይንገዋለላል።

5 የሸክላ ሠሪው ሥራ በእሳት፥ ሰውም በአነጋገሩ ይፈተናል።

6 ዛፉ የሚበቅልበት የአትክልት ሥፍራ፥ በሚያፈራው ፍሬ ይመዘናል፤ የሰዎችንም ስሜት ቃላቸው ያጋልጣል።

7 ቃሉን ሳትሰማ ሰውን አታሞግስ፤ ሰው የሚፈተነው በአነጋገሩ ነውና።


ጽድቅ

8 ጽድቅን ብትከተል ታገኛታለህ፤ እንደ ክቡር ካባም ትጐናጸፋታለህ።

9 ወፎች ከመሰሎቻቸው ጋር ይኖራሉ፤ እውነት ወደሚሿት ሰዎች ትመጣለች።

10 አንበሳ ግዳይ ለመጣል ያደፍጣል፤ ኃጢአትም እንዲሁ በደለኞችን ያጠምዳል።

11 የጻድቅ ሰው ንግግር ምንም ጊዜ ጥበብ ነው፤ ሞኝ ሰው ግን እንደ ጨረቃ ተለዋዋጭ ነው።

12 ጅሎችን ስትጐበኝ ተገቢውን ሰዓት ምረጥ፤ ከአስተዋዮች ዘንድ ግን ስለ ጊዜ አታስብ።

13 የሞኞችን ንግግር ያስቀይማል፤ በፈጸሙትም ኃጢአት እያጓሩ ይስቃሉ፤

14 መሐላ የሚያበዙ ሰዎች ንግግር ፀጉር ያቆማል፤ ጩኸታቸውም ጆሮ ያስይዛል፤ ስድባቸውም ለሰማ አስደንጋጭ ነው።

15 የኩራተኞቹ ፍልሚያ በደም መፋሰስ ይደመደማል፤ እርግማናቸውም ለመስማት በጣም ያሳፍራል።


ምሥጢሮች

16 ምሥጢሮችን የማይጠብቅ መታመንን ያጣል፤ የሚሻውንም ወዳጅ አያገኝም።

17 ወዳጅህን ውደደው፥ እመነውም፤ ምሥጢሮቹን ካወጣህ ግን ዳግም አትቅረበው፤

18 ሰውን ገድሎ ማጥፋት እንደሚቻል ሁሉ፥ የጐረቤትህንም ወዳጅነት አንተ ገድለኸዋልና።

19 ከእጅህ እንዳመለጠች ወፍ፥ እንዲሁ ባልንጀራህ አምልጦኃል፤ ዳግመኛም ልትይዘው አትችልም።

20 አትከተለው፤ ከወጥመድ እንደምታመልጥ ሚዳቋም ሸሽቷል።

21 ቁስል ይሸፍናል፤ ለስድብም ይቅርታ ይደረጋል፤ ምሥጢር ለሚያወጣ ግን አንዳች ተስፋ የለም።


ግብዝነት

22 ዓይኑን የሚጨነቁር ተንኮል ያጠነናል፤ ይህን ከማድረግ የሚያግደው የለም።

23 በፊትህ ንግግሩ አንደ ማር ይጣፋጣል፤ ያንተንም በአድናቆት ያዳምጣል። ከኋላህ የሚያወራው ግን ፈጽሞ ሌላ ነው፤ ቃልህንም መሰናክል ያደርገዋል።

24 በርካታ ነገሮችን እጠላለሁ፤ እንደ እርሱ የሚሆን ግን ከቶ የለም፤ እግዚአብሔርም እርሱን ይጠላዋል።

25 ድንጋይ የሚወረውር በራሱ ላይ ይጥለዋል፤ የክሕደት ቡጢ በሁለት አቅጣጫ ይቆርጣል።

26 ጉድጓድ የሚቆፍር በውስጡ ይገባል፤ ወጥመድ ያጠመደም ራሱ ይጠመዳል።

27 ክፉ በሚሠራ ክፉ ይወርድበታል፤ አመጣጡንም አያውቀውም።

28 አሽሙርና ስድብ የግትር ሰው ምልክቶች ናቸው፤ በቀል ግን እንደ አንበሳ አድፍጦ ይጠብቀዋል።

29 በጻድቅ ሰው ውድቀት በማደሰቱት ላይ ወጥመድ ይወድቅባቸዋል፥ ከሞታቸውም በፊት ሥቃይ ይጨርሳቸዋል።


ምሬት

30 ምሬትና ቁጣ ከንቱ ነገሮች ናቸው፤ ኃጢአተኛውም ሰው በእነርሱ ሠልጥኗል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች