ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የጥበብ ንግግር 1 ጥበብ ራሷን ታሞግሳለች፤ በተከታዮቿም ዘንድ በራሷ ትከበራለች። 2 በልዑል እግዚአብሔር ጉባኤም ትናገራለች፤ በኃያሉ አምላክ ፊት ክብርን ታገኛለች። 3 እኔ ከልዑል እግዚአብሔር አፍ ወጣሁ፥ ዓለምንም እንደ ጉም ሸፈንኋት፤ 4 በሰማያት ድንኳኔን ዘረጋሁ፤ ዙፋኔም የደመና ምሰሶ ነበር። 5 ብቻዬን ሰማያትን የዞርሁ፥ በጥልቁም ጉድጓድ የተጓዝሁ እኔ ነኝ። 6 በባሕር ማዕበሎችና በመላዋ ምድር፥ በሕዝቦችና በሀገሮች ሁሉ ላይ ሥልጣኔ የተዘረጋ ነበር። 7 በእነርሱም መካከል ላርፍ ፈለግሁ፥ ስፍሬንም የት እንደማደርግ ተመለከትሁ። 8 በዚያን ጊዜ የሁሉ ነገር ፈጣሪ አዘዘኝ፥ እኔን የፈጠረኝ ለድንኳኔ ሥፍራ አዘጋጅ። ድንኳንሽን በያዕቆብ ትከይ፥ ርስትሽንም በእስራኤል አድርጊ አለኝ። 9 ከሁሉ አስቀድሞ እኔን ከዘላለማዊነት ፈጠረ፤ ለዘለዓለምም እኖራለሁ። 10 በተቀደሰው ድንኳን በእርሱ ፊት እገለገልሁ፤ ማደሪያዬንም በጽዮን አደረግሁ። 11 በተወደደችው ከተማ አሳረፈኝ፤ ሥልጣኔንም በኢየሩሳሌም አሳየሁ። 12 የአምላክ ንብረትና ውርሱ በሆኑት፥ በተመረጡት ሕዝቦች ዘንድ ሠራን ሰደድሁ። 13 እንደ ሊባኖስ ዝግባ መስሎ፥ በሔርሞን ተራራ እንደሚገኘው ጥድም ታላቅ ሆንሁ። 14 እንደ ኤን-ገዳ ዘንባባና፥ እንደ ኢያሪኮ ጽጌረዳም አደረግሁ፥ በሜዳ እንደ በቀለ ውብ ወይራ፥ እንደ ለውዝ ዛፍም ተንዥረገግሁ። 15 እንደ ቀረፋ፥ እንደ ሜሮንም ዛፍ፥ መልካም መዓዛዬን ሰጠሁ፤ እንደ ምርጥ ከርቤ፤ እንደ ልባንጃ ጥሪኝና ኦኒካ እንደሚባል ሽቶ፥ በድንኳኑ እንደሚጨሰው ዕጣንም፥ ጣፋጭ ሽዬን ታገሥሁ። 16 ቅርንጫፎቼን እንደ ቱሪማንትሪ ዘረጋሁ፤ እነርሱም ክብርና ሞገስ ያላቸው ናቸው። 17 እኔ እንደሚንዠረገግ ሐረግ ነኝ፤ አበቦቼም የክብርና የሀብት ፍሬዎች ተሸክመዋል። 19 የምትፈልኝ ቅረቡኝ፤ ክፍሬዎቼም ያሻችሁን ያክል ውሰዱ። 20 ትዝታዬ ከማር ይጣፍጣል፤ እኔን መውረስ ከማር ወለላ ይመረጣል። 21 እኔን የሚመገቡ ይበልጥ ይራባሉ፤ እኔን የሚጠጡ ይበልጥ ይጠማሉ። 22 ትእዛዜን የሚፈጽም አያፍርም፤ እኔ የማዘውን የሚያደርግ ከቶውንም ኃጢአት አይሠራም። ጥበብና ሕግ 23 ይህ ሁሉ የልዑል እግዚአብሔር የቃል ኪዳን መጽሐፍ ነው። ለእኛ ለያዕቆብ ቤተሰቦች በሙሴ አማካኝነት የተሰጠን ሕግ ነው። 25 ጥበብን እንደ ፌቮን፥ በፍሬ ወቅት እንደሚፈሰው የጤግሮስ ወንዝ የሚያጥለቀልቃት፥ 26 እውቀትን እንደ ኤፍራጥስ፥ በመከር እንደሚሞላው የዮርዳኖስ ወንዝ የሚያጥለቀልቃት፥ 27 ምክርንም እንደ ዓባይ የሚያፈስ፥ በወይን ለቀማ ወቅት እንደ ግዮን የሚያንዠረዥረው የሙሴ ሕግ ነው። 28 የመጀመሪያው ሰው ጠንቅቆ ሊያውቃት አልቻለም፤ የመጨረሻውም አላገኛትም። 29 ሐሳብዋ ከባሕር የሰፋ፥ ትልሟም ከጥልቅም ጥልቅ ነውና። 30 እኔም እንደ መስኖ ቦይ፥ ወደ አትክልት ሥፍራም እንደሚፈስ የውሃ መስመር፥ 31 አትክልቱን ውሃ አጠጣለሁ፤ አበባዎቼን በመስኖ አለማለሁ አልሁ፤ እነሆ መስኖዬ ወንዝ፥ ወንዜም ባሕር ሆነ። 32 ከንጋት ጀምሮ ምክር እንዲያበራ፥ ብርሃኑንም በስፋትና በርቀት እንዲፈነጥቅ አደርጋለሁ። 33 ትምህርት እንደ ትንቢት፥ የወደፊት ትውልዶች ውርስ ይሆን ዘንድ እጥራለሁ። 34 እነሆ አስተውሉ! ለግሌ ብቻ ሳይሆን ጥበብን ለሚሹ ሁሉ ስል ደክሜያለሁ። |