ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 አባቴና የሕይወቴ መሪ ጌታ ሆይ፥ ለእነርሱ ፈቃድ እንድገዛ አትተወኝ፤ ይጠሉኝም ዘንድ አትፍቀድ። 2 ሐሳቤን የሚሸነቁጥልኝ፥ የጥበብንም ሕግ በልቤ የሚያስረጽ፥ ስሕተቶቼን ፈጽሞ የማያልፍ፥ ኃጢአቴንም የሚመረምር እርሱ ከቶ ማነው? 3 ስህተቶቼ እንዳይበዙ፥ ኃጢአቴ እንዳይከመር፥ በጠላቶቼ ፊት እንዳልወድቅና ድሉም የእነርሱ ሆኖ እንዳይፈነጥዙ፥ 4 አባቴ፥ የሕይወቴ አምላክ ጌታዬ ሆይ! ለዐይኖቼ ትዕቢትን አትስጥ። 5 ምቀኝነትን ከእኔ ዘንድ አርቅ፥ 6 ፍትወትና ለሥጋ ምኞት አታስገዛኝ፥ ወሰን ላጣ ፍላጐት አሳልፈህ አትስጠኝ። መሐላ 7 ልጆች ሆይ! ትምህርቴን አድምጡ፥ እርሱን የሚፈጽም ከቶውንም በወጥመድ አይገባም። 8 ኃጢአተኛው በከናፍሩ ተጠምዷል፤ ተሳዳቢውና ትዕቢተኛውም በእነርሱ ተጠልፎ ይወድቃል። 9 መሐላ አይልመድብህ፥ የቅዱስ እግዚአብሔርን ስም በዋዛ አትጥራ። 10 በቅርብ የሚቆጣጠሩት አገልጋይ ሰንበር እንደማያጣው ሁሉ፥ በእርሱ የሚምልና ስሙንም የሚጠራ ሰው ከቶውንም ከኃጢአት አይነጻም። 11 ሁልጊዜ የሚምል ሰው በኃጢአት የተሞላ ነው፤ ምንጊዜም ከቤቱ መቅሠፍት አይጠፋም። እርሱ ከበደለ ኃጢአቱ በራሱ ላይ ይወድቃል፤ ካለመጠንቀቅ የፈጸመው ከሆነ ደግሞ፤ ኃጢአቱ ድርብ ይሆንበታል። በሐሰት ከማለ ይቅርታ አይደረግለትም፤ ቤቱም በመቅሠፍት ይሞላል። ጸያፍ ንግግር 12 እንደ ሞት ያለ ንግግር አለ፤ ከቶ ይህን የመሰለ አነጋገር በያዕቆብ ዘር አይገኝ። 13 ግርድፍና ጸያፍ ቋንቋን በአንደበትህ አታስለምድ፤ ኃጢአትን ያዘው ቃላት ናቸውና። 14 በታላላቆች መሀል ስትቀመጥ አባትና እናትህን አስብ፤ በውስጣቸው መኖርክን ዘንግተህ፥ የሞኝ ባሕርይ እዳታሳይ ተጠንቀቅ፥ ይህን ብታደርግ አለመፈጠርህን ትመኛለህ፤ የተወለድክበትንም ቀን ትረግማለህ። 15 ጸያፍ ቋንቋን የአፍ መፍቻው ያደረገ፥ በሕይወት እስካለ ድረስ ራሱን ከዚህ ስሕተት ሊያርቅ አይችልም። አመንዝራነት 16 ኃጢአትን በኃጢአት ላይ የሚፈጽሙ ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፤ ሦስተኛው ደግሞ ቁጣን ያመጣል። 17 እንደ ምድጃ ላይ እሳት የሚንቀለቀል ፍላጐት፤ እስካልረካ ድረስ አይጠፋም። ሥጋውን ለፍትወት የሚመኝ፥ እስኪቃጠል ድረስ ምኞቱ አይቆምም። ለሚልከሰከስ ምግብ ሁሉ ጣፋጭ ነው፤ እስኪሞት ድረስ ከዚያ አይርቅም። 18 በትዳሩ ላይ የሚባልግ፥ ማን ያየኛል? በጨለማ ተከብቤያሁ፥ በግድግዳዎችም መሀል ተከልያለሁ፥ ማንም ስለማያየኝ ከቶ የሚያስጨንቀኝ ምንድነው? ልዑል እግዚአብሔር ኃጢአቴን አይዘክረውም ብሎ ያስባል። 19 እሱ የሚፈራው የሰዎችን ዐይን ነው፤ የእግዚአብሐርን ዐይኖች ዐሥር ሺህ ጊዜ ከፀሐይ የበሩ መሆናቸውን ግን አይገነዘብም። የሰውን ባሕርይ እጅግ ሥውር መሸሸጊያዎችንም ሳይቀር ዘልቆ እንደሚያይ አልተከሠተለትም። 20 ከመፈጠራቸው በፊት ለእርሱ ሁሉም ይታወቃሉ፤ ከተፈጠሩ በኋላ ዛሬም ያውቃቸዋል። 21 ይህ ሰው በከተማው ሕዝብ ፊት ይቀጣል፥ ባልጠበቀበትም ጊዜ ይያዛል። ዘማዊት 22 ለባሏ የማትታመንና ወራሹን ከሌላ የምትወልድለት ሴትም፥ ቅዥትዋ እንዲሁ ይሆናል። 23 በመጀመሪያ የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ አፍርሳለች፥ ሁለተኛ በባሏ ላይ ወስልታለች፤ ሦስተኛ በዝሙት አድፋ 24 ከሌላ ወንድ ፀንሳለች፤ በጉባኤ ፊት ትቀርባለች፤ ስለ ልጅችዋም ትጠይቃለች፤ 25 ልጆችዋ ሥር አይኖራቸውም፥ ቅርንጫፎቿም ፊጽሞ አይጠፋም። 26 የተረገመ ትውስት ትታ ታልፋለች፤ እፍረቷም ፈጽሞ አይጠፋም። 27 ያዩዋትም ሁሉ እግዚአብሔርን ከመፍራት የበለጠ ነገር እንደሌለ ይገነዘባሉ፤ ትእዛዛትን መፈጸምም ከሁሉ የተሻለ መሆኑን ይረዳሉ። |