ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 22 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሀኬተኛ ሰው 1 ሀኬተኛ ሰው በቁሻሻ እንደተሸፈነ ድንጋይ ነው፤ ሁሉም በቆሻሻነቱ ይንቀዋል፤ 2 ሀኬተኛ ሰው እንደ ግፍ ነው፤ የሚነካው ሁሉ እጁን ያፈናጥቃል። መጥፎ ልጆች 3 በጐ አስተዳደግ የጐደለው ልጅ አባት መሆን አሳፋሪ ነው፤ ሴት ልጅ መውለድ ግን ታላቅ ኪሣራ ነው። 4 አስተዋይ ልጅ ባል ታገኛለች፤ እፍረተ ቢሷ ልጅ ግን የወላጅዋ ኀዘን ናት። 5 ደፋር ሴት ልጅ እናትና አባቷን ታሳፍራለች፤ በሁለቱም ዘንድ ትተዋለች። 6 ያለ ጊዜው የሚከሰት እምቢተኛነት በቀብር ላይ እንደሚሰማ ሙዚቃ ነው፤ ሁልጊዜ መቅጣትና ማረም ግን ጥበብ ነው። ጥበብና ሞኝነት 9 ሞኝን ማስተማር የተሰባበሩ ገሎችን እንደ መጠገን ነው፤ ጽኑ እንቅልፍ የያዘውንም ሰው እንደ መቀስቀስ ነው። 10 ሞኝን ማስተማር ለተኛ ሰው እንደ ማውራት ነው፤ በጨረስህም ጊዜ ነገሩ ምንድነው? ይልሃል። 11 ብርሃኑን ላጣው ለዚያ ለሞተ ሰው አልቅስ፤ አእምሮው ላጣው ለዚያ ለሞኝ ሰው አልቅስ። ለሞተውና ላረፈው ብዙ እንባ አታፍስ፤ የሞኝ ሕይወት ከሞት የከፋ ነውና። 12 ለሙታን የሚታዘነው ለሰባት ቀናት ነው፤ ለሞኞችና ለክፉዎች ግን ዕድሜ ልካቸውን ይታዘንላቸዋል። 13 ከአላዋቂ ሰው ጋር ንግግር አታብዛ፤ ከጅልም አትጠጋ። እርሱን ተጠንቀቀው፥ አልያ ግን ችግር ላይ ትወድቃለህ። ከእርሱም ጋር በመነካካትህ ታድፋለህ። ከእርሱ ራቅ፥ የአእምሮ ሰላምም ታገኛለህ፤ በጅል ተግባሩም አትሸማቀቅም። 14 ከእርሳስ የሚከብድ ምን አለ? ከሞኝ በቀር ሌላስ ስም አለውን? 15 አሸዋ፥ ጨውና የብረት ቁራጭ ከጅል ሰው የቀለሉ ሸክሞች ናቸው። 16 ከሕንጻው ጋር የተያየዘ ማገር መሬት ብትንቀጠቀጥም ቦታውን አይለቅም። አስቦበት የቆረጠ ልብም እንደዚሁ በቀውጢ ሰዓት አይብረከረክም። 17 በበቃ ማስተዋል ላይ የተገነባ ልብ፥ በተስተካከለ ግድግዳ ላይ እንደሚደረግ ጌጥ ነው። 18 በግምብ ላይ የተቀመጡ ጠጠሮች ንፋሱን መቋቋም አይችሉም፤ በገዛ ሐሳቡ ፍርሃት ያደረበት የሞኝ ልብም እንዲሁ ፍርሃትን አይቋቋምም። ወዳጅነት 19 ዐይን ብትጠነቁል እምባ ይፈሰዋል፥ ልብን ብተነካካው ደግሞ ስሜቶቹን ትገልጣለህ። 20 በወፎች ላይ ድንጋይ ብትወረውር ታባርራቸዋልህ፤ ወዳጅህን ብትገሥጽ ደግሞ ወዳጅነትን ታጠፋለህ። 21 በባልንጀራህ ላይ ሠይፍህን ብትመዝ፥ መመለሻ መንገድ ስላለው ተስፋን አትቁረጥ፤ 22 ባልንጀራህ ላይ ክፉ ብትናገር እርቅ ይወርደ ዘንድ ተስፋ ስላለ አትጨነቅ፤ ብትሰድበው፥ ሐሳበ-ግትር ብትሆንበት፥ ምሥጢሩን ብትገልጽበትና ከጀርባው ብትወጋው ግን ባልንጀራህን እንደምታጣ እወቅ። 23 ጐረቤትህ በደኸየ ጊዜ ታማኝነትህን አሳየው፥ ባገኘ ጊዜም አብረኸው መደሰት ትችላለህና። ከውርሱም ድርሻውን ታገኝ ዘንድ፤ በችግሩ ጊዜ ከጐኑ አትለይ። 24 የእሳት መኖር በምድጃውና በጭሱ ጠረን እንደሚታወቀው፥ ደም መፍሰስም እንዲሁ በፀያፍ ቃል ይታወቃል። 25 ባልንጀሪዬን ለማስጠጋት አላፍርም፤ ከእርሱም ፊት አልደበቅም። 26 በእርሱም አማካኝነት ክፉ ቢደርስብኝ፤ ይህን የሰማ ሁሉ ከእርሱ ይጠነቀቃል። ጸሎት 27 በአፌ ላይ ዘብ የሚያቆም፤ በከንፈሮቼ ላይ የሚያትም፥ እንዳልወድቅና በምሳሌም ሰበብ እንዳልጠፋ የሚጠብቀኝ ከቶ ማን ይሆን? |