ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ልዩ ልዩ ኃጢአቶች 1 ልጄ ሆይ ኃጢአት አድርገሃልን? ዳግመኛ አታድርግ፥ ስላለፈውም ስሕተትህ ይቅርታ ጠይቅ። 2 ከእባብ እንደምትሸሽ እንዲሁ ከኃጢአት ሽሽ፤ ከተጠጋህ ይነድፍሃል፤ ንጉሦቹ እንደ አንበሳ ጥርሶች ናቸው። የሰውንም ሕይወት ያጠፋሉ። 3 ሕግን ማፍረስ በሁለት በኩል ስለት እንዳለው ሰይፍ ነው፤ በሰይፉ የተመታ ቁስሎቹ አይሽሩም። 4 ሽብርና ዓመጽ ሃብትን ያምሳሉ፥ እንዲሁ የትዕቢተኛ ቤትም ይጠፋል። 5 የደኃን ልመና እግዚአብሔር ፈጥኖ ይሰማል፤ የእርሱም ፍርድ ሳይዘገይ ይደርሳል። 6 ተግሣጽን የሚጠላ የኃጢአተኛን ፈለግ ይከተላል፤ ጌታን የሚፈራ ግን በልቡ ይጸጸታል። 7 አፈ ጮሌው በሁሉም ዘንድ ይታወቃል፤ ጥንቁቅ ግን ምንም አያመልጠውም። 8 በሌላ ሰው ገንዘብ ቤቱን የሚሠራ ለመቃብሩ ድንጋይ እንደሚሰበስብ ሰው ነው። 9 የኃጢአተኞች ጉባኤ እንደ ገለባ ክምር ነው፤ ፍጻሜአቸው በሚንቦገቦግ እሳት ውስጥ ይሆናል። 10 የኃጢአተኞች መንገድ ለስልሶ የተነጠፈ ነው፤ መጨረሻው ግን የሲኦል ጉድጓድ ነው። ጥበበኛና ሞኝ ሰው 11 ሕግን የማያከብር ሰው ሐሳቡን መቆጣጠር ይችላል፤ እግዚአብሔር መፍራት መጨረሻው ጥበበን ማግኘት ነው። 12 ተፈጥሮአዊ ችሎታ የሚጐድለው ሰው ለመማር አይበቃም፤ አንዳንድ ክህሎቶች ግን ምሬትን ያመጣሉ። 13 የጠቢቡ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ፥ ምክሩም እንደማይደርቅ ምንጭ ነው። 14 የሞኝ ልብ እንደ ሽንቁር ማሰሮ ነው። ምንም ዓይነት ትምህርት አይዝም። 15 የተማረ ሰው የጥበብ ምሳሌ ሲሰማ ያደንቃል፤ የራሴንም ያክልበታል። ባካኝ ሰው ቢሰማው ግን አይወደውም፤ ሊያስታውሰውም አይሻም። 16 የሞኝ ንግግር እንደ የመንገድ ላይ ሸክም ነው፤ አዋቂን ማድመጥ ግን ደስታ ነው። 17 በጉባኤ ውስጥ የብልጡ ሰው ንግግር በጉጉት ይጠበቃል፤ ለንግግሩም ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። 18 የሞኝ ጥበብ እንደ ቤት ፍርስራሽ ያለ ነው፤ የማይረባ ሰው ዕውቀት ውል የሌለው ንግግር ነው። 19 ለማያመዛዝን ሰው ትምህርት ሰው ትምርት በእግር ላይ እንደሚገባ እግረ-ሙቅ፥ በቀኝ እጅም ላይ እንደሚታሰር ሰንሰለት ነው። 20 ሞኝ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጐ ይስቃል፤ አዋቂ ሰው ግን ያለ ድምፅ ፈገግ ይላል። 21 ለአዋቂ ሰው ትምህርት እንደ ወርቅ ጌጥ፥ እንደ እጅ አምባርም ነው። 22 ሞኝ ሰው እግሮቹን ወደ ቤት ለማስገባት ይጣደፋል፤ አዋቂ ሰው ግን በትሕትና ቀስ ብሎ ይገባል። 23 ጋጠ-ወጡ በበር ቀዳዳ ያሾልቃል፥ ጨዋ ሰው ግን ከበር ይጠብቃል። 24 በበር አጠገብ ቆሞ ማዳመጥ የመጥፎ አስተዳደግ ምልክት ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከቶውንም ይህን አያደርግም። 25 የአሉባልተኞች ከንፈር ሌሎች የተናገሩትን ይደግፋል፤ የአዋቂ ሰው ንግግር የተመዘነ ነው። 26 የሞኞች ልብ በአፋቸው፥ የአዋቂዎች አፍ ግን በልባቸው ውስጥ ነው። 27 ክፉ ሰው ሰይጣንን ሲረግም ራሱን መርገሙ ነው። 28 ሐሜተኛ ሰው ራሱን ያዋርዳል፤ የጐረቤቱቹንም ጥላቻ ያተርፋል። |