ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ዝምታና ንግግር 1 ያ ጊዜው የሚሰነዘር ተግሣጽ አለ፤ ዝምተኛ ሰው አለ፥ እርሱም ብልጥ ነው። 2 በቁጣ ከመንደድ መገሠጽ ምንኛ የተሻለ ነው! 3 ጥፋቱን የሚያምን ከቅጣት ይድናል። 4 ፍትሕን በኃይል ለመጫን የሚሻ ሰው፥ ልጃገረድን ለመድፈር እንደሚሞክር ጃንደረባ ነው። 5 ዝምተኛ ሰው እንደ ጥበበኛ ይቆጠራል፤ ብዙ በመናገሩ ደግሞ የሚጠላ ሰው አለ። 6 አንዳንዱ ሰው መልስ ስለሌለው ዝም ይላል፤ ሌላው ደግሞ መች እንደሚናገር ስለሚያውቅ ዝም ይላል፤ 7 ወቅቱ እስኪደርስ ብልህ ሰው በዝምታው ይቀጥላል፤ ለፍላፊው ሞኝ ግን ይህን አይረዳም። 8 ብዙ የሚናገር ይጠላል፥ የማይገባውን ሥልጣን የያዘም ሰው አይወደድም። ተፃራሪ አባባሎች 9 አንዳንዱን መከራ ይጠቅመዋል፤ ዕድላምነቱም ያከስረዋል። 10 ምንም ጥቅም የማይሰጥ አንዳንድ ስጦታ አለ፤ እጥፍ ድርብ ጥቅም የሚያስገኝ ስጦታም አለ፤ 11 አንዳንድ ጊዜ ክብር ለውርደት ይዳርጋል፤ የተዋረዱም ሰዎች እራሳቸውን ያቀናሉ። 12 አንዳንድ ሰው በጥቂት ገንዘብ ብዙ ነገሮች ይበዛል፤ ሆኖም ግን ሰባት እጥፍ ይከፍልበታል። 13 ጥበበኛው በቃሉ ይፈቀራል፥ አላዋቂው ግን በከንቱ ስጦታዎችን ያፈሳል። 14 የአላዋቂ ሰው ሰጦታ ምንም አይጠቅምህም፤ ዐይኖቹ ሰባት ጊዜ እጥፍ ምላሽን ይጠብቃሉበና። 15 ጥቂት ይሰጣል፤ ብዙ ይነቅፋል፤ እንደ አዋጅ ነጋሪ አፉን በሰፊው ይከፍታል። ዛሬ አበድሮ በነጋታው ክፍያን ይጠይቃል፤ እንዲህ ያለ ሰው በጣም የተጠላ ነው። 16 ሞኝ ወዳጅ የለኝም፤ በመልካም ሥራዎቼ የሚያመሰግነኝ ማንም የለም፤ 17 እንጀራዬን የሚበሉ ሰዎች ነገረኛ ምላስ አላቸው ይላል። ስንቴ በስንቶቹ ይሳቅበት ይሆን! የማይገባ ንግግር 18 ምላስ ከሚያዳልጥ በመንገድ ዳር መውደቅ ይሻላል፤ ኃጢአተኞች ሳያስቡት የሚወድቁት እንዲሁ ነው። 19 ያልታረመ ደንቆሮ ሰው ደጋግመው እንደሚያወሱት ታሪክ ውል የሌለው ነው። 20 ሞኝ በተገቢው ወቅት የማይናገር በመሆኑ፤ ከእርሱ የሚመነጭ ምሳሌም ተቀባይነትን አያገኝም። 21 ማጣት ከኃጢአት የሚጠብቀው ሰው አለ፤ የሕሊና ጸጸትም ዕረፍት አይነሳውም። 22 እውነተኛ ካልሆነ ዕረፍት በመነሣት በራስ ላይ ጥፋትን የሚጋብዝ አለ፤ ስለ ሞኞቹ አስተያየት ሲል እንዲሁ የሚጠፋ አለ። 23 እውነተኛ ያልሆነ ዕረፍት ለወዳጅ የተስፋ ቃል የሚሰጥና ሳይቸግረው ጠላት የሚገዛም አለ። መዋሸት 24 መዋሸት በሰው ላይ የሚሳፍር ዕድፍ ነው፤ ባልተገራ አፍ ላይ ሁልጊዜ ውሸት ይገኛል። 25 ልማደኛ ዋሾ ከመሆን ይልቅ ሌባ መሆን ይሻላል፥ ሁለቱም ግን የሚያመሩት ወደ ጥፋት ነው። 26 ውሸት የሚጠላ ባሕሪ ነው፤ የውሸታም ውርደት ዘላለማዊ ነው። ጥበብ 27 ጥበበኛ የሚሻሻለው በቃላት ነው፤ ብልጥ ደግሞ በታላላቆች ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል። 28 መሬቱን የሚያርስ መኸሩን ያፍሳል፤ ከታላላቆች ዘንድ የተጠጋ ስለጥፋቱ ይቅርታን ያገኛል። 29 እጅ መንሻና መማለጃ ስጦታ የጥበበኞችን ዐይን ይሸፍናል፤ ተግሣጽንም በአፍ ላይ እንደተደገነ አፈ ሙዝ ያፍናል። 30 ጥበብ ከተደበቀ፥ ሀብትም ካልታወቀ፥ የሁለቱስ ቢሆን ጥቅማቸው ከምኑ ላይ ነው? 31 ጥበቡን ከሚደብቅ ሰው፥ ሞኝነቱን የሚሸፍን ሰው ይበልጣል። |