ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የእግዚአብሔር ታላቅነት 1 ዘላለማዊው አምላክ ሁሉንም ፈጠረ፥ ትክክለኛውም ዳኛ እርሱ ብቻ ነው። 2 ጻድቅ የሚባል እግዚአብሔር ብቻ ነው። 4 ለማንም ቢሆን ሥራዎቹን ሁሉ የማወቅን ሥልጣን አልሰጠም፥ ድንቅ ሥራዎቹንስ ሊመረምር የሚችል ማን ነው? 5 ወሰን የሌለው ኃያልነቱን የሚገመግም ማን ነው። ስለ ምሕረቶቹስ ዘልቆ መናገር የሚችልስ አለን? 6 ከምሕረቱ ላይ መቀነስ ወይም መጨመር አይቻልም፤ የጌታን ተአምራት ጠልቆ ለማየት አይሞከርም። 7 ሰው ጨረስኩ ሲል ገና መጀመሩ ነው፤ ምርምሩንም ሲያበቃ፥ እንቆቅልሹ ሲጀምር እንደነበረው ነው። የሰው ከንቱነት 8 ሰው ምንድነው? ለምንስ ይጠቅማል? የሚጠቅመውና የሚጐደውስ ምንድነው? 9 የሕይወቱ ርዝማኔ ቢበዛ መቶ ዓመት ነው። 10 ከዘላለማዊነት ጋር ሲነጻጸሩ እኒህ ዓመታት ከባሕር እንደ ተገኘ ውሃ ጠብታ ወይም እንደ አንዲት አሸዋ ይቆጠራል። 11 ስለዚህ ነው እግዚአብሔር ለሰዎች ትዕግሥተኛ የሆነውና ርኀራኄውንም የሚያደርግላቸው። 12 የሰውን ልጆች ፍጻሜ አስከፊነት የሚያውቀውና የተገነዘበው በመሆኑ፥ ይቅርታውን ያበዛል። 13 የሰው ርኀራኄ ለባልንጀራው ነው፤ እግዚአብሔር ግን ለፍጥረት ሁሉ ይራራል፥ ይገሥጻል፥ ያርማል፥ ያስተምራል፥ እረኛ መንጋውን እንደሚመልስ፥ እሱም ወደ መንገድ መልሶ ያገባል። 14 ምክሩን ለሚቀበሉና ውሳኔውን በትጋትና በጥንቃቄ ለሚፈልጉ ሰዎች ይራራላቸዋል። የመስጠት ጥበብ 15 ልጄ ሆይ ነቀፌታ የሚያስከትለውን ደግ ነገር አድርግ፤ በስጦታዎችህ ላይ አሳዛኝ ቃላት አታደባልቅ። 16 ጤዛ ሙቀትን አይቀንስምን? ቃልም እንደዚሁ ከስጦታ ይልቃል። 17 በርግጥም መልካም ቃል ከታላቅ ስጦታ የተሻለ ነው፤ ቸር ሰው ግን ሁለቱንም ለመስጠት ዝግጁ ነው። 18 አላዋቂ ሰው ቢያቀርብም ዘለፋን ነው፤ የሚያስቆጭ ስጦታ ደግሞ ዐይኖችን ያስለቅሳል። ማሰላሰልና አርቆ መመልከት 19 ከመናገርህ በፊት ተማር፥ ከመታመምህ በፊት ተጠንቀቅ። 20 ከፍርድ ቀን በፊት እራስህን መርምር፥ በጉብኝቱም ቀን ነጻ ትሆናለህ። 21 ከመታመምህ በፊት ትሕትናን ተላመድ፥ ኃጢአት እንደፈጸምክ ተጸጸት። 22 ቃል ከመግባትህ በፊት እራስህን አዘጋጅ፤ እግዚአብሔርን እንደሚያስቀይሙት ሰዎች አትሁን፤ 23 ቃል ከመግባትህ በፊት እራስህን አዘጋጅ፤ ጌታን እንደሚፈታተኑት ሰዎች አትሁን፤ 24 በመጨረሻው ቀን የሚመጣውን ቅጣት አስታውስ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወዲያ ሲመልስ የሚወርደውን ቁጣ አስብ። 25 በጥጋብ ጊዜ የራብ ዘመንን አስታውስ፤ ሀብታምም ባትሆን ድኀነትንና ማጣትን አስብ። 26 ንጋትና ምሽት ሲፈራረቁ ጊዜው ያለፋል፤ ላምላካችን ሁሉም ቶሎ ያልፋል። 27 ጥበበኛ ሰው በሁሉ ነገር ይጠነቀቃል፤ እግዚአብሔርን ላለማስቀየምም፥ በበደል ወቅቶች እራሱን ይጠብቃል። 28 አስተዋይ ሰው ሁሉ ጥበብን ያውቃታል፤ እርሷንም ያገኘውን ያከብራል። 29 ያነጋገር ለዛዎችን የሚገነዘቡ፥ ስለ ጥበብ ተግተው ሠርተዋል፤ ትክክለኛ ምሳሌዎችንም አንቆርቁረዋል። ራስን መግዛት 30 ለስሜቶችህ ተገዢ አትሁን፥ ፍላጎቶችህንም ግታ። 31 ፍላጎቶችህን ካረካህ፥ የጠላቶችህ መሳቅያ ትሆናለህ። 32 በምቾት ኑሮ አትንደላቀቅ፥ ከዚህም ማኀበር አትደባለቅ። 33 ኪስህ ባዶ ሆኖ በብድር ብትፈነጭ፥ እራስክን ታደኸያለህ። |