Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


እውነተኛ ደስታ

1 በንግግሩ ያልተሳሳተ ሰው፥ ስለ ኃጢአትም መጸጸት የማያስፈልገው የተባረከ ነው።

2 ኀሊናው የማይወቅሰውና በተስፋ የኖረ ሰው የተባረክ ነው።

3 ለንፉግ ሃብት አይገባውም፤ ለቀናተኛስ ንብረት ምን ያደርግለታል?

4 በመስቀንቀን ሃብት የሚያከማች ለሌሎች ያጠራቅማል፤ እነርሱም በእርሱ ሃብት ይንደላቀቃሉ።

5 ለገዛ ራሱ ክፉ የሆነ ማንን ይጠቅማል? የራሱ የሆነውን እንኳ አይደሰትበትም።

6 የገዛ ራሱን ከሚጐዳ ሰው የባሰ ክፉ አይገኝም፤ እነሆ የክፋቱን ዋጋ እንደዚሁ ያገኛል።

7 ደግ እንኳ ቢሠራ ፈቅዶ የሚያደርገው አይደለም፤ በመጨረሻም ክፋቱ ይገለጥበታል።

8 ቀናተኛ ዐይን ያለው ሰው መጥፎ ነው፤ ስለሌሎች ሕይወት አይጨነቅም፤ ፊቱንም ይመልስባቸዋል።

9 የንፉግ ሰው ዐይን ባለው አይረካም፤ ንፍገትም ነፍሱን ያኮማትራታል።

10 ንፉግ ሰው ለእንጀራ ይሳሳል፤ በማዕዱም ጥጋብ የለም።

11 ልጄ ሆይ በሚቻልህ መጠን ራስህን በመልካም አስተዳድር፤ ለእግዚአብሐርም የተገባውን መባ አቅርብ።

12 ሞት ሳትዘገይ እንደምትመጣ አስታውስ፤ የሲኦልን ውል አይተህ አታውቅምና፤

13 ከመሞትህ በፊት ለወዳጅህ ደግ ነገር አድርግለት፤ እንደተቻለህ በደግነት አስተናግደው።

14 የዛሬው ደስታ አያምልጥህ፤ ከተገቢው ደስታ ድርሻህ አያምልጥህ።

15 የደከምህበትን ፍሬ ለሌላ ትተወው የለምን? የድካምህን ፍሬ ዕጣ እንዲጣጣሉበት ታደርግ የለምን?

16 ስጥ፥ ተቀበልም፥ ራስህን አስደስት፤ በሲኦል የሚገኙ ደስታዎች የሉምና።

17 እንደ ልብስ ሁሉ ሥጋም ያረጃል፤ ቋሚው ሕግ “ሁሉም ይሞታል” የሚለው ነው።

18 ቅርንጫፉ በበዛ ዛፍ ላይ እንደሚበቅል ቅጠል፥ አንዳንዶቹ ይወድቃሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ያድጋሉ፤ የሥጋና የደም ትውልዶች እንደዚሁ ናቸው፤ አንዱ ሲሞት ሌላው ይወለዳል።

19 ሰው የሠራው ነገር ሁሉ ይበሰብሳል፥ ይጠፋል፤ ሰሪውም እንዲሁ ያልፋል።


የጠቢቡ ደስታ

20 ጥበብን የሚማርና አእምሮው እንዲመራመር የሚያደርግ ሰው የተባረከ ነው።

21 በልቡ የጥበብን መንገድ የሚያሰላስልና ምሥጢሯንም ጠልቆ የሚመረምር እርሱ የተመረቀ ነው።

22 እንደሚያድን ሰው ይከተላታል፥ በመንገዷም አድፍጦ ይጠብቃል፤

23 በመስኮቶችዋም ይቃኛል፤ በደጃፍዋ ሆኖ ያዳምጣል።

24 በቤትዋም አጠገብ ይቀመጣል፤ ችካሉንም በግንቦቿ ሥር ይተክላል።

25 በአጠገቧ ድንኳኑን ይተክላል፤ ውብ በሆነም ስፍራ ይኖራል።

26 ልጆቹን በእርሷ ጥላ ሥር ያስቀምጣል፤ ከቅርንጫፎቿም በታች ይኖራል።

27 ከሐሩሩ ይጠለልባታል፤ በሞገሷም ቤቱን ይሠራል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች