Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የደግነት ሕግጋት

1 ደግ ነገር ስታደርግ ለማን እንደምታደርገው ዕወቅ፤ ደግ ሥራዎችህ በከንቱ አይቀሩም።

2 ለጻድቅ ሰው መልካምን አድርግ፤ ዋጋህን ታገኛለህ፤

3 በክፉ ነገር ጸንቶ የሚኖር ሰው ደስታ አያገኝም፤ ምጽዋት ማድረግ የማይፈልግ ደስታ የለውም።

4 ለጻድቅ ሰው ስጥ፤ ግን ኃጢአተኛን ከቶ አትርዳ።

5 ለትሑት ሰው ደግ አድርግ፥ ለክፉ ሰው ምንም አትስጥ፤ እንጀራም ከልክለው፥ ምንም አትስጠው፥ ከሰጠኸው ግን በአንተ ላይ ኃይል ያገኛል፤ ባደረግህለት ደግ ሥራ ሁሉ ዕጥፍ ክፋት ያደርግብሃል።

6 ልዑል እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ይጠላል፤ ለክፉዎች የሚገባቸውን ቅጣት ይሰጣቸዋል።

7 ለደግ ሰው ስጥ፤ ኃጢአተኛን ግን አትርዳ።


እውነተኛና ሐሰተኛ ወዳጅ

8 በደስታ ጊዜ ትክክለኛ ወዳጅን መለየት አትችልም፤ በመከራ ጊዜ ግን ጠላትህን አትስተውም።

9 አንድ ሰው ሲሳካለት ጠላቶቹ ይሆናሉ፤ ሁሉም ነገር ሲበላሽበት ደግሞ ወዳጁ እንኳ ይርቀዋል።

10 ጠላትህን ከቶ አትመነው፤ ነሐስ እንደሚዝግ፥ የጠላትህም ተንኮል እንደዚያው ይሆናል።

11 ትሑት ቢመስልና አንገቱን ቢደፋም፥ ቁጥብነትህን ግፋበት፤ ጥንቃቄም አድርግበት፥ በሱ ዘንድ መስተዋት እንደሚወለውል ሁን፤ ዝገቱም እስከ መጨረሻም እንደማይዘልቅ እወቅ።

12 ከአጠገብህ አታስቁመው፤ ገፍትሮህ ቦታህን ሊይዝ ይችላልና፤ ወንበርህን እንዳይቀማህ በቀኝህ አታስቀምጠው፤ የንግግሬን ትክክለኛነት በመጨረሻ ትገነዘበዋለህ፤ በመጸጸት ቃሎቼን ታስታውሳቸዋለህ።

13 በእባብ ለተነከሰው አስማተኛ፥ ከጨካኝ አውሬዎችስ ጋር ለሚውል ማን ያዝንለታል?

14 የኃጢአተኛን ወዳጅ የሚሆንና ተባባሪውም የሚሆን እንዲሁ ነው።

15 ለአጭር ጊዜ ከአንተ ጋር ይቆያል፤ መንገድ ከከፍትክለት ግን ጥቅሙን ያሳድጋል።

16 ጠላት ንግግሩ ጣፋጭ ሊሆን ይችላል፤ ልቡ ደግሞ አንተን ወደ ጉድጓድ የሚጥልበት ውጥን ይዟል። የአዞ ዕንባ ሊያነባ ይችላል፤ አጋጣሚውን ካገኘ ግን የደም ጥሙ አይረካም።

17 መከራ ቢወድቅብህ ከፊትህ ቀድሞ ይገኛል፤ የሚረዳህም መስሎ ያደናቅፍሃል።

18 ራሱን ይነቀንቃል፤ ያጨበጭባል፤ ብዙ ያንሾካሹካል ገጹም ይለወጣል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች