Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሲራክ 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የመልክ አታላይነት

1 ጥበብ ደሃውን ታኰራዋለች፤ ከታላላቆችዋ ጋር ታስቀምጠዋለች፤

2 ስለ ውበቱ ማንንም አታመስግን፤ በመልኩ ማንንም አትጥላ።

3 ከበራሪ ፍጡራን ታናሺቱ ንብ ናት፤ ምርቷ ግን ከጣፋጮች ጣፋጭ ነው።

4 ሰዎች ሲያከብሩህ አትኩራ፤ የእግዚአብሔር ሥራዎች ድንቅ ነገር ግን ለሰዎች ድብቅ ናቸው።

5 በርካታ ነገሥታት ተዋርደው በምድር ላይ ተቀመጠዋል፤ ያልተጠበቀው ሰውም ዘውድን ተቀዳጅቷል።

6 ብዙ ባለ ሥልጣኖች በፍጹም ተዋርደዋል፤ ዝነኞች የነበሩ ሰዎች በሌሎች እግር ሥር ወድቀዋል።


ማመዛዘንና ማሰላሰል

7 ጉዳዩን ከመገንዘብህ በፊት ሰውን አትንቀፍ፤ አስቀድመህ አስብ፤ በኋላ ንቀፍ።

8 መልስ ከመስጠትህ በፊት አድምጥ፤ በሰው ንግግር መካከል ጣልቃ አትግባ።

9 በማያገባህ ጉዳይ አትከራከር፤ በኃጢአተኞች ፀብ ውስጥ አትግባ።

10 ልጄ ሆይ ከአቅምህ በላይ ሥራ አታብዛ፤ ፍላጎቶችህ ቢበዙ ስለ እነርሱ ትቸገራለህ፤ ብትሮጥም አትደርስም፤ ብትሸሽም አታመልጥም።

11 አንዳንዶች በፍጥነት ጠንክረው ይሠራሉ፤ እራሳቸውን የሚያገኙት ግን ጭራ ሆነው ነው።


በእግዚአብሔር ብቻ እመን

12 አንዳንዶች እርዳታ የሚሹ ደካሞች ናቸው። ንብረት የሌላቸው እና በድኀነት የበለጸጉ ናቸው። እግዚአብሔርም ዐይኑን ወደ እነርሱ ይመልሳል። ከገቡበትም አዘቅት ያወጣቸዋል።

13 ራሳቸውን ቀና ያደርግላቸዋል፤ ብዙዎች በነሱ ይደነቃሉ፤

14 ጥሩና መጥፎ፤ ሕይወትና ሞት፤ ድኀነትና ሀብት ሁሉም ከእግዚአብሔር የሚገኙ ናቸው።

17 በእግዚአብሔር ለታመኑ ስጦታው አይነጥፍም፤ እርዳታውም ሁሌ ከእነርሱ ጋር ነው።

18 ሌሎች በንፍገት ሀብት ያከማቻሉ፤ ታዲያ ዋጋቸው ምን እንደሆነ እነሆ ተመልከቱ፤

19 ሰው “ዕረፍት አግኝቻለሁ፤ አሁን ያለኝን እየበላሁ እኖራለሁ” ሲል ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አያውቅም፤ ገንዘቡን ለሌሎች ትቶ ይሞታል።

20 ሥራህን አጥብቀህ ያዝ በርትተህም ሥራ፤ በሥራህም ጸንተህ አርጅ።

21 በኃጢአተኛ ሥራ አትደነቅ፤ በእግዚአብሔር ተማመን፤ በሥራህ ጸንተህ ኑር፤ በድንገት ባንድ አፍታ ድኃውን ማበልጸግ ለእግዚአብሔር ቀላል ነውና።

22 የጻድቅ ሰው ዋጋው የእግዚአብሔር ቡራኬ ነው፤ እግዚአብሔር ባንድ ጊዜ ቡራኬውን እንዲያብብ ያደርገዋል።

23 “ምን የሚቸግረኝ ነገር አለ? ለወደፊት ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልገኛል?” አትበል።

24 “የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ አለኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምን መከራ ይመጣብኛል?” አትበል።

25 በደስታ ቀን ክፉ ነገር ይረሳል፤ በመከራ ቀን ደስታ አይታወስም።

26 በሞት ጊዜ ለያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን መክፈል ለእግዚአብሔር ቀላል ነው።

27 ቅጽበታዊ መከራና ደስታ ይረሳሉ፤ በሰው የሕይወቱ የመጨረሻ ሰዓት የሠራው ሁሉ ይገለጣል።

28 ሰውን ከመሞቱ በፊት የታደለ ነው አትበለው፤ እርሱን የምታውቀው ሲሞት ነውና።


ክፉን ሰው አትመን

29 ሁሉንም ሰው ወደ ቤትህ አታምጣ፤ አብዛኞቹ የተንኮለኞች ወጥመድ ናቸውና።

30 የትዕቢተኛ ልብ በጐጆዋ ውስጥ በወጥመድ እንደ ተያዘች ቆቅ ነው፤ እንደ ሰላይ ውድቀትህን ይጠባበቃል።

31 ሁሌም ስለሚከታተልህ ደጉን ወደ ክፉ ይለውጣል፤ ድንቅ የሚሰኝለትንም ሥራ አቃቅር ያወጣለታል።

32 ምድጃ ሙሉ ፍም ከሰል የሚቀጣጠለው፥ ከአንድ ብልጭታ ነው፤ ኃጢአተኛው ደም ለማፍሰስ ተዘጋጅቶ ይጠባበቃል።

33 ከክፉ ሰው እና ከሴራዎቹ ተጠበቅ፤ ለዘለዓለም ሊያጠቃህ ይችላልና።

34 ባዕድ ሰው ብታስጠጋ ችግር ይፈጥርብሃል፤ ከቤተሰብህም ያለያይሃል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች