ሮሜ 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ወንድሞች ሆይ! የልቤ መልካም ምኞትና እግዚአብሔርንም የምለምነው እስራኤላውያን እንዲድኑ ነው። 2 ለእግዚአብሔር ቅንዓት እንዳላቸው እመሰክርላቸዋለሁ ነገር ግን ቅንአታቸው በእውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም። 3 የእግዚአብሔርን ጽድቅ ባለማወቅ፥ የራሳቸውንም ጽድቅ ለመመሥረት በመፈለግ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። 4 የሚያምን ሁሉ እንዲጸድቅ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። መዳን ለሁሉም 5 ሙሴ በሕግ ስለ ሆነው ጽድቅ ሲጽፍ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። 6 ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፥ “በልብህ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤” ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7 ወይም “በልብህ ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤” ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማስነሣት ነው። 8 ነገር ግን ምን ይላል? ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ነው፤ የምንሰብከው የእምነት ቃል ይህ ነው። 9 ምክንያቱም ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር፥ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ፤ 10 ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፥ በአፉም መስክሮ ይድናልና። 11 መጽሐፍ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም” ይላልና። 12 በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ልዩነት የለምና፤ ያው ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ 13 “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።” 14 ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት ይጠሩታል? ያልሰሙትንስ እንዴት ያምኑታል? ያለ ሰባኪስ እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? 15 ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ? “መልካሙን ዜና የሚያበሥሩ እግሮቻቸው እንዴት ውብ ናቸው!” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 16 ነገር ግን ሁሉም ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ “ጌታ ሆይ! የተናገርነውን ማን አመነ?” ብሏልና። 17 ስለዚህ እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው፤ መስማትም በክርስቶስ ቃል በኩል ነው። 18 ነገር ግን አልሰሙም ወይ? እላለሁ፥ በእርግጥም ሰምተዋል፤ “ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።” 19 ነገር ግን እስራኤል አላወቀምን? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ “ሕዝብ ባልሆነው አስቀናችኋለሁ፤ በማያስተውል ሕዝብም አስቆጣችኋለሁ” ብሏል። 20 ስለዚህ ኢሳይያስም በድፍረት “ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ” አለ። 21 ስለ እስራኤል ግን “ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ” ይላል። |