ራእይ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት 1 “በኤፌሶን ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚመላለሰው እንዲህ ይላል፦ 2 “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንደማትችል፥ እንዲሁም ሐዋርያት ሳይሆኑ ‘ነን’ የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ 3 በትዕግስት መጽናትህንና ስለ ስሜ መከራ መቀበልህን አውቃለሁ። 4 ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና። 5 እንግዲህ ከየት እንደ ወደቅህ አስብ፤ ንስሓም ግባ፥ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሓም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ። 6 ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔም የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ትጠላለህ። 7 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ። ለሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት 8 “በሰምርኔስም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ሞቶ የነበረው፥ ሕያውም የሆነው፥ ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል፦ 9 “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ የሚሉት፥ ይልቁንም የሰይጣንም ማኅበር የሆኑት፥ የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ። 10 የሚጠብቅህን መከራ አትፍራ። እነሆ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያስገባ ነው፤ ለዐሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። 11 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም። ለጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት 12 “በጴርጋሞንም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል፦ 13 “የት እንደምትኖር አውቃለሁ፥ የሰይጣን ዙፋን ባለበት ነው፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፤ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ በእኔ ያለህን እምነት አልካድህም። 14 ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ፤ ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር አሉና። 15 እንዲሁም የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ። 16 እንግዲህ ንስሓ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፤ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ። 17 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፤ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፤ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም ተጽፎአል። ለትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት 18 “በትያጥሮንም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዐይኖች ያሉት በምድጃም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፦ 19 “ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንደሚበዛ አውቃለሁ። 20 ዳሩ ግን ‘ነቢይ ነኝ’ የምትለውን፥ ባርያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ስለምትላት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ 21 ንስሓም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሓ መግባትን አልወደደችም። 22 እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርሷም ጋር የሚያመነዝሩትንም ከሥራዋ ንስሓ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፤ 23 ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ፥ ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። 24 ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ፥ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁት ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፤ 25 ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ። 26-27 ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፤ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ 28 የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ። 29 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።” |