ራእይ 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የመጨረሻዎቹን መቅሰፍቶች የያዙ መላእክት 1 ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ቁጣ በእነርሱ ስለሚፈጸም ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ታዩ። 2 በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባሕር የሚመስለውን አየሁ፤ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቍጥር ላይ ድል ነሥተው የነበሩት የእግዚአብሔርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባሕር ላይ ሲቆሙ አየሁ። 3-4 “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! መንገድህ ትክክልና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ! የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፤ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ፤” እያሉ የእግዚአብሔርን ባርያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ። 5 ከዚህም በኋላ አየሁ፤ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፤ 6 ሰባቱንም መቅሠፍት የያዙ ሰባቱ መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ ንጹሕ የጌጥ ልብስ ለበሱ፤ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ። 7 ከአራቱም ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሚኖረው እግዚአሔር ቁጣ የተሞሉትን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው። 8 ቤተ መቅደሱ ከእግዚአብሔር ክብርና ከኀይሉ የተነሣ በጢስ ተሞላ፤ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ ማንም ወደ መቅደሱ መግባት አልቻለም። |