Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 91 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።

2 ጌታን፦ “አንተ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ ነህ እለዋለሁ”፥ የምታመንበት አምላኬ ነውና።

3 እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና።

4 በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ ከክንፎቹም በታች ትጠለላለህ፥ ታማኝነቱ እንደ ጋሻና እንደ ቅጥር ይከብብሃል።

5 ከሌሊት ሽብር፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥

6 በጨለማ ከሚጓዝ መቅሰፍት፥ በቀትር ከሚደመስስ አደጋ አትፈራም።

7 በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም ዐሥር ሺህ ይወድቃሉ፥ ወደ አንተ የሚጠጋ የለም።

8 በዐይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ቅጣት ታያለህ።

9 ጌታን፥ “አንተ ተስፋዬ ነህ” ብለህ፥ ልዑልን መጠጊያህ አድርገሃልና።

10 ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም።

11 በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፥

12 እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።

13 በተኩላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፥ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ።

14 በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፥ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ።

15 ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፥ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ።

16 ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች