መዝሙር 85 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ለመዘምራን አለቃ፥ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 2 አቤቱ፥ ምድርህን በመልካም ጎበኘህ፥ የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ። 3 የሕዝብህን በደል አስቀረህ፥ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይቅር አልክ። 4 መዓትህንም ሁሉ አስወገድህ፥ ከቁጣህ መቅሠፍት ተመለስህ። 5 የመድኃኒታችን አምላክ ሆይ፥ መልሰን፥ ቁጣህንም ከእኛ መልስ። 6 በውኑ ለዘለዓለም ትቈጣናለህን? ቁጣህንስ ለልጅ ልጅ ታስረዝማለህን? 7 አቤቱ፥ ሕይወትን ልትሰጠን አትመለስምን? ሕዝብም በአንተ ደስ ይላቸዋል። 8 አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህን አሳየን፥ አቤቱ፥ ማዳንህንም አሳየን። 9 እግዚአብሔር የሚናገረውን እሰማለሁ፥ ወደ እብደታቸው ካልተመለሱ በቀር ጌታ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ይናገራልና። 10 ነገር ግን ክብር በምድራችን ያድር ዘንድ ማዳኑ ለሚፈሩት ቅርብ ነው። 11 ጽኑ ፍቅርና እውነት ተገናኙ፥ ጽድቅና ሰላም ተቃቀፉ። 12 እውነት ከምድር በቀለች፥ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች። 13 ጌታም በጎ ነገርን ይሰጣል፥ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች። 14 ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፥ የእርምጃውንም ዱካ በመንገድ ውስጥ ያኖራል። |