Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 81 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ለመዘምራን አለቃ፥ በዋሽንት፥ የአሳፍ መዝሙር።

2 ለኃይላችን ለእግዚአብሔር በደስታ ዘምሩ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ።

3 ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር፥

4 በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፥

5 ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፥ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ።

6 ከግብጽ በወጣ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክር አድርጎ አቆመው። ያላወቅሁትን ቋንቋ ሰማሁ።

7 ጫንቃውን ከሸክም፥ እጆቹንም በቅርጫት ከመገዛት አራቅሁ።

8 በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ አዳንሁህም፥ ከተሰወረ የሞገድ ስፍራ መለስሁልህ፥ በክርክር ውኃ ዘንድም ፈተንሁህ።

9 ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ እነግርሃለሁም፥ እስራኤል ሆይ፥ ምነው በሰማኸኝ!

10 አንተስ ብትሰማኝ ሌላ አምላክ አይሆንልህም፥ ለሌላ አምላክም አትሰግድም።

11 ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ ጌታ አምላክህ ነኝና፥ አፍህን አስፋ እሞላዋለሁም።

12 ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም፥ እስራኤልም አላዳመጠኝም።

13 እንደ ልባቸው ሥራ ተውኋቸው፥ በልባቸውም አሳብ ሄዱ።

14 ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን፥ እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን፥

15 ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር፥ በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር፥

16 የጌታ ጠላቶችም በተገዙለት ነበር፥ ዘመናቸውም ለዘለዓለም በሆነ ነበር፥

17 ከስንዴም ስብ ባበላኋቸው ነበር፥ ከዓለቱም ማር ባጠገብኋቸው ነበር።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች