መዝሙር 66 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ለመዘምራን አለቃ፥ የመነሣት የምስጋና መዝሙር። 2 በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥ ለስሙም ዘምሩ፥ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ። 3 እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፦ “ሥራህ እንዴት ግሩም ነው፥ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ። 4 በምድር ያሉ ሁሉ ለአንተ ይሰግዳሉ፥ ለአንተም ይዘምራሉ፥ ለስምህም ይዘምራሉ።” 5 ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፥ ከሰው ልጆች ይልቅ በግብሩ ግሩም ነው። 6 ባሕርን የብስ አደረጋት፥ ወንዙንም በእግር ተሻገሩ፥ በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል። 7 በኃይሉ ለዘለዓለም ይገዛል፥ ዐይኖቹ ወደ አሕዛብ ይመለከታሉ፥ ዓመፀኞች ራሳቸውን ከፍ ከፍ አያድርጉ። 8 አሕዛብ ሆይ፥ አምላካችንን ባርኩ፥ የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ። 9 ነፍሴን በሕይወት ያኖራታል፥ እግሮቼንም ለመናወጥ አልሰጠም። 10 አቤቱ፥ ፈትነኸናልና፥ ብርንም እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና። 11 ወደ ወጥመድ አገባኸን፥ በጀርባችንም መከራን አኖርህ። 12 ሰው በራሳችን ላይ እንዲረማመድ አደረግህ፥ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥ ወደ በረከትም አወጣኸን። 13-14 ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ወደ ቤትህ እገባለሁ፥ በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን በከንፈሮቼም ቃል የገባሁልህን ስእለቴን እፈጽማለሁ። 15 ከወጠጤዎች መዓዛ ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ፍሪዳን አቀርባለሁ፥ ላሞችንና ፍየሎችን እሠዋልሃለሁ። 16 እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሁሉ፥ ኑ፥ ስሙኝ፥ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ። 17 በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፥ በአንደበቴም አመሰገንሁት። 18 በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። 19 ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ፥ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ። 20 ጸሎቴን ያልከለከለኝ ቸርነቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን። |