Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 56 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ለመዘምራን አለቃ፥ ከቅዱሳን ስለ ራቁ ሕዝብ፥ ፍልስጥኤማውያን በጋት በያዙት ጊዜ፥ የዳዊት ቅኔ።

2 አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፥ ሁልጊዜም ተዋጊ አስጨንቆኛል።

3 የሚዋጉኝ በዝተዋልና ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ።

4 እኔ ግን ፈራሁ በአንተም ታመንሁ።

5 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፥ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፥ ሥጋ ምን ያደርገኛል?

6 ሁልጊዜ ቃሎቼን ይጠመዝዙብኛል፥ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው።

7 ይሸምቁብኛል ይሸሸጋሉ፥ ተረከዜን ይከታተላሉ፥ ነፍሴንም ለማጥፋት ይጠብቃሉ።

8 መቼም አታድናቸውም! አቤቱ አሕዛብን በቁጣ ጣላቸው።

9 አምላክ ሆይ፥ መዋተቴን ነገርሁህ፥ እንባዬን በአቁማዳ ውስጥ አኑር።

10 በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፥ አንተ አምላኬ ከእኔ ጋር እንደሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ።

11 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፥ በጌታ ቃሉን እወድሳለሁ።

12 በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል?

13 አቤቱ፥ በአንተ ዘንድ ሰእለት አለብኝ፥ የምስጋና መሥዋዕት አቀርብልሀለሁ፥

14 ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን በእግዚአብሔር ዘንድ እመላለስ ዘንድ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች