መዝሙር 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ከልጁ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸ ጊዜ የዳዊት መዝሙር። 2 አቤቱ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ! በኔ ላይ የሚቆሙት ብዙ ናቸው። 3 ብዙ ሰዎች ነፍሴን፦ አምላክሽ አያድንሽም አልዋት። 4 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ጋሻዬ ነህ፥ ክብሬና ራሴንም ቀና የምታደርገው አንተ ነህ። 5 በሙሉ ድምጽ ወደ ጌታ እጮሃለሁ፥ ከተቀደሰ ተራራውም ይሰማኛል። 6 እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም፥ ጌታም ደግፎኛልና ነቃሁ። 7 የሚከቡኝን አእላፍ ሕዝብ አልፈራም። 8 ተነሥ፥ አቤቱ፥ አምላኬ ሆይ፥ አድነኝ፥ አንተ የጠላቶቼን መንጋጋ መትተሃልና፥ የክፉዎችንም ጥርስ ሰብረሃልና። 9 ማዳን የጌታ ነው፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው። |