መዝሙር 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የዳዊት መዝሙር። 1 የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ። 2 አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፥ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ። 3 አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፥ በከንቱ የሚከዱ ያፍራሉ። 4 አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፈለግህንም አስተምረኝ። 5 አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፥ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ። 6 አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና። 7 የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፥ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ። 8 ጌታ ቸርና ቅን ነው፥ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል። 9 ትሑታንን በፍርድ ይመራል፥ ለትሑታን መንገድን ያስተምራቸዋል። 10 የጌታ መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ። 11 አቤቱ፥ በደሌ ብዙ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ። 12 ጌታን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ እርሱን ያስተምረዋል። 13 ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል። 14 ጌታ ለሚፈሩት ወዳጃቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል። 15 እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዐይኖቼ ሁልጊዜ ወደ ጌታ ናቸው። 16 እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ መልስ ማረኝም። 17 የልቤ ችግር ብዙ ነው፥ ከጭንቀቴ አውጣኝ። 18 ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ። 19 ጠላቶቼ እንደበዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል። 20 ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፥ አንተን ታምኛለሁና አልፈር። 21 አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና ፍጽምናና ቅንነት ይጠብቁኝ። 22 አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው። |