Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 145 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


1 የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

1 የዳዊት የምስጋና መዝሙር። አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ስምህንም ለዘለዓለም ዓለምም እባርካለሁ።

2 በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም ለዘለዓለም ዓለምም አመሰግናለሁ።

3 ጌታ ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፥ ታላቅነቱም የማይመረመር ነው።

4 ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ።

5 የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፥ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ።

6 የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፥ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ይነጋገራሉ።

7 የቸርነትህን ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ።

8 ጌታ ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቁጣ የራቀ፥ ጽኑ ፍቅሩም ብዙ ነው፥

9 ጌታ ለሁሉም ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው።

10 አቤቱ፥ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።

11 የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፥ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፥

12 ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ

13 መንግሥትህ የዘለዓለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።

14 ጌታ በቃሎቹ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፥ ጌታ የሚወድቁትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ ያጎነበሱትንም ያነሣቸዋል።

15 የሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፥ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ።

16 አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።

17 ጌታ በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።

18 ጌታ ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።

19 ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያሳካል፥ ጩኸታቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም።

20 ጌታ የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፥ ክፉዎችንም ሁሉ ያጠፋል።

21 አፌ የጌታን ምስጋና ይናገራል፥ ሥጋም ሁሉ ለዘለዓለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች