መዝሙር 109 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። 1 ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። አምላክ ሆይ፥ ምስጋናዬን ዝም አትበል፥ 2 የክፉና የተንኰለኛ አፎች በላዬ ተላቅቀውብኛልና፥ በሐሰት አንደበትም በላዬ ተናገሩ፥ 3 በጥላቻ ቃል ከበቡኝ፥ በከንቱም አጠቁኝ። 4 በፍቅሬ ፋንታ ከሰሱኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ። 5 በመልካም ፋንታ ክፉን፥ በፍቅር ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ። 6 በላዩ ክፉ ሰውን ሹም፥ ሰይጣንም በቀኙ ይቁም። 7 በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፥ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት። 8 ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፥ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ። 9 ልጆቹም ያለ አባት ይቅሩ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን። 10 ልጆቹም እጅጉን ይቅበዝበዙ፥ ይለምኑም፥ ከፈራረሱ ቤቶቻቸውም ሳይቀር ይባረሩ። 11 ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት። 12 በቸርነት የሚያግዘውንም አያግኝ፥ ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር። 13 ተተኪ አይኑረው፥ በቀጣይ ትውልድ ስማቸው ይደምሰስ። 14 የአባቶቹ ጥፋት በጌታ ፊት ትታወስ፥ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ። 15 በጌታ ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ፥ መታሰቢያቸውም ከምድረ ገጽ ይጥፋ። 16 በቸርነት ለመመላለስ አላሰበምና፥ ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ለመግደል ያሳድድ ነበር። 17 መራገምን ወደደ፥ ወደ እርሱም መጣች፥ በረከትንም አልመረጠም፥ ከእርሱም ራቀች። 18 መራገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች። 19 እንደሚለብሰው ልብስ፥ ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ትሁነው። 20 ይህ ቅጣት በሚከሱኝና በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ላይ ከጌታ ዘንድ ይሁን። 21 አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ ስትል ታደገኝ፥ ጽኑ ፍቅርህ መልካም ናትና አድነኝ። 22 እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና፥ በውስጤም ልቤ ቆስሎአል። 23 እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥ እንደ አንበጣም እረገፍሁ። 24 ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፥ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ። 25 እኔም በእነርሱ ዘንድ መሳለቂያ ሆንሁ፥ ሲያዩኝ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። 26 አቤቱ አምላኬ፥ እርዳኝ፥ እንደ ጽኑ ፍቅርህም አድነኝ። 27 አቤቱ፥ እጅህ ይህች መሆኗን፥ አንተም ይህንን እንዳደረግህ ይወቁ። 28 እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ትባርካለህ፥ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ፥ አገልጋይህ ግን ደስ ይበለው። 29 የሚከሱኝ እፍረትን ይልበሱ፥ እፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት። 30 ጌታን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ፥ 31 ነፍሱን ከሚያሳድዱአት ያድን ዘንድ ከድሀ በኩል ቆሞአልና። |