ምሳሌ 31 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 እናቱ ያስተማረችው የማሣ ንጉሥ፥ የልሙኤል ቃል። 2 ልጄ ሆይ፥ ምንድነው? የሆዴ ልጅ ሆይ፥ ምንድነው? የስእለቴ ልጅ ሆይ፥ ምንድነው? 3 ጉልበትህን ለሴቶች አትስጥ፥ መንገድህንም ነገሥታትን ለሚያጠፉ። 4 ለነገሥታት አይገባም፥ ልሙኤል ሆይ፥ ነገሥታት የወይን ጠጅ ሊጠጡ፥ መሳፍንትም፦ ብርቱ መጠጥ ወዴት ነው? ሊሉ አይገባም፥ 5 ጠጥተው ሕግን እንዳይረሱ፥ የድሀ ልጆችንም ፍርድ እንዳያጐድሉ። 6 ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፥ 7 ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጉስቁልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ። 8 ስለ ዲዳው ተናገር፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ። 9 ተናገር፥ በእውነትም ፍረድ፥ ለድሀና ለምስኪን ፍረድ። 10 ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቁ እጅግ ይበልጣል። 11 የባሏ ልብ ይታመንባታል። መልካም ነገር አይጐድልበትም። 12 ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም። 13 የበግ ጠጉርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች። 14 እርሷ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፥ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች። 15 ገና ሳይነጋ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለአገልጋዮችዋም ሥራ ትሰጣለች። 16 እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፥ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች። 17 ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥ ክንድዋንም ታበረታለች። 18 ማትረፍዋን ታስተውላለች፥ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም። 19 እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ። 20 እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች። 21 ለቤትዋ ሰዎች ብርድን አትፈራም፥ የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ የለበሱ ናቸውና። 22 ለራስዋም የአልጋ ልብስ ትሠራለች ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች። 23 ባሏ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ይሆናል። 24 የበፍታ ልብስ እየሠራች ትሸጣለች፥ ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች። 25 ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፥ በሚመጣውም ዘመን ላይ ትስቃለች። 26 በጥበብ ትናገራለች፥ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ። 27 የቤትዋንም ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፥ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም። 28 ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጉን ነሽ ይሏታል፥ ባሏ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል፦ 29 “መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።” 30 ደም ግባት ሐሰት ነው፥ ውበትም ከንቱ ነው፥ ጌታን የምትፈራ ሴት ግን እርሷ ትመሰገናለች። 31 ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፥ ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት። |